በሀዋሳ ዓመታዊው የቅዱስ ገብርኤል የንግስ በዓል በሠላም እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል

110

ሃዋሳ ፤ታህሳስ 16/2014(ኢዜአ) በሃዋሳ ከተማ ዓመታዊው የቅዱስ ገብርኤል የንግስ በዓል በሠላም እንዲከበር አስፈላጊ ዝግጅት መደረጉን የሲዳማ ክልል የፀጥታ አካላት አስታወቁ።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ተስፋዬ ቱንጋሞ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በመጪው ማክሰኞ የሚከበረው የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ የንግስ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲከበር ፖሊስ የቅድመ ዝግጅት ሥራውን እያገባደደ ነው።  

ከሀገር ውስጥና ከውጭ  የሚመጡ የእምነቱ ተከታዮችና ጎብኚዎች በዓሉን በሠላም አክብረው ወደ መጡበት እንዲመለሱ የፖሊስ አባላት የጸጥታውን ሥራ በተቀናጀና በተናበበ አግባብ እንዲያስፈጽሙ ስምሪት መሰጠቱንም አመልክተዋል፡፡

የፀጥታውን ሥራ ህዝባዊ መሰረት ለማስያዝ የተለያዩ የጸጥታ አካላትንና የማህበረሰብ ክፍሎችን ያቀፈ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ከኮሚሽኑ ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታን ባገናዘበ መልኩ የክልሉ ነዋሪዎች ከጸጥታ ሃይሉ ጋር በተቀናጀ መልኩ ሰላማቸውን እያስጠበቁ መሆኑንም ኮሚሽነር ተስፋዬ ተናግረዋል።

የሲዳማ ክልል ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቴዎስ በበኩላቸው፤ በንግስ በዓሉ ወቅት ፀረ ሠላም ኃይሎች ችግር እንዳያደርሱ ህብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር የአካባቢውን ደህንነት በንቃት እንዲጠብቅ አሳስበዋል።

በተለይ አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎችን ሲመለከት በአቅራቢያው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥ ነው ያመለከቱት።

"በዓሉ በሰላም  እንዲከበርም ከሃይማኖት መሪዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው" ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት የሚመጡ ዲያስፖራዎች ሃይማኖታዊ በዓላትን ከማክበር ጎን ለጎን  በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን በመጎብኘት የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ አስተማማኝ የፀጥታ ስራ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።

ዓመታዊውን የቅዱስ ገብርኤል የንግስ በዓል በታላቅ ድምቀት ለማክበር ግብረ ሃይል ተቋቁሞ የዝግጅት ሥራው እየተገባደደ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሲዳማ  ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቢ ጥበባት ቀሲስ ሞላልኝ መርጊያ ናቸው።

በተለይ የጸጥታውን ሥራ ለማጠናከር የቤተክርስቲያን ወጣቶችና የሰንበት ተማሪዎች ከከተማዋ አስተዳደርና ማህበረሰብ ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን  አስረድተዋል።

በንግስ በዓሉ ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው ስለሚመጣ ምዕመናኑ በዓሉ በሚከበርበት አካባቢ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል መጠቀምና አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ታህሳስ 19  በሃዋሳ ከተማ በደማቅ ሁኔታ ለሚከበረው የቅዱስ ገብርኤል ንግስ በዓል በሠላም መጠናቀቅም ምዕመኑ ለፀጥታ አካላት ተባባሪ እንዲሆን መጋቢ ጥበባት ቀሲስ ሞላልኝ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም