ነጻ በወጡ አካባቢዎች በወንጀል ተጠያቂ የሆኑ አካላትን ለፍትሕ ለማቅረብ እየተሰራ ነው

76

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከአሸባሪው ህወሃት ነጻ በወጡ የአማራና አፋር ክልል አካባቢዎች በወንጀል ተጠያቂ የሆኑ አካላትን ለፍትሕ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን መንግሥት አስታወቀ።

የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ በሰጡት መግለጫ “የተመድ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጋር ባከናወኑት ምርመራ ውጤትና ምክረ ሃሳብ መሰረት መንግስት የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል” ብለዋል።

መልሶ ግንባታና አገልግሎቶችን ከማስጀምር ጎን ለጎን በወንጀል ተጠያቂ የሆኑ አካላትን ለፍትሕ ለማቅረብ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቀዋል።

“በወራራ ተይዘው በነበሩ አካባቢዎች የተፈጸሙ ወንጀሎችን የሚመረምር የወንጀል ምርመራና የማስቀጣት ቡድን በፍትሕ ሚኒስቴር በኩል ተቋቁሞ የምርመራ ስራው ተጀምሯል” ብለዋል።

“የምርመራ ቡድኖቹ በአሸባሪው ህወሃት ተይዘው በነበሩ የአማራና አፋር ክልል አካባቢዎች ከባለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ የደረሱትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ወንጀሎችን የሚያሳይ ተጨባጭ መረጃ ለማግኘት በሚያስችል መልኩ ቅኝት ለማድረግ ተሰማርተዋል” ነው ያሉት።

በሽብር ቡድኑ የተፈጸሙ የንጹሃን ዜጎች ሕይወት መጥፋትን፣የአካል መጉደልን፣ የአስገድዶ መድፈር ወንጀልን፣ ከቤት ንብረት መፈናቀልን፣ የንብረት ውድመትን፣የመንግስታዊ ተቋማት ሰነዶች ውድመት እና ሌሎች እጅግ ዘግናኝ ወንጀሎችን ለማጣራት እነዚህ የመርማሪ ቡድኖች ተሰማርተዋልም ሲሉ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በአፋር ክልል መርማሪ ቡድን መሰማራቱንና በስሩ ሁለት ንዑሳን ቡድኖችን ይዞ ምርመራ እያከናወኑ ይገኛል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ።

“በአማራ ክልል ደግሞ በርካታ ቡድኖች መሰማራታቸውን አንስተው ሸዋሮቢትን ጨምሮ በሰሜን ሸዋ ዞን በአስር ወረዳዎች፣ በደቡብ ወሎ ስምንት ወረዳዎች፣ የኦሮሞ ልዩ ዞን አካባቢዎች፣ በደሴና ኮምቦልቻ፣ ጋሸናን ጨምሮ በሰሜን ወሎ ዞን ምርመራና ምልከታዎችን ለማድረግ ቡድኖቹ ተሰማርተዋል” ብለዋል።

ከነዚህ አካባቢዎች በተጨማሪ ቡድኖቹ ወደ ዋግህምራ አካባቢዎችና ወደ ወልድያ መሰማራታቸውንም አንስተዋል።

ምርመራዎቹና ምልከታዎቹ የሚካሄዱት በአሸባሪው ህወሃት የተካሄዱትን ጥፋቶች በተጨባጭና በሁለንተናዊ መልኩ ማሳየት በሚችሉበት ደረጃ እንደሆነም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም