ኢትዮጵያ እውነታዋን ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭው ማሕበረሰብ በሚገባ ማስረዳት እንድትችል ጠንካራ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ግንባታ ሥራ እየተሰራ ነው

254

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ)  ኢትዮጵያ እውነታዋን ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭው ማሕበረሰብ በሚገባ ማስረዳት እንድትችል ጠንካራ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ግንባታ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በይዘት፤ በድምጽና ምስል ቀረጻ፣ በአርትኦት እንዲሁም በተቋማዊ ብራንዲንግ ዘርፍ ከተለያዩ የፌዴራል ተቋማት ለተውጣጡ የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎች ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቋል።

በሥልጠናው ማጠቃለያ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አስተባባሪ ሚኒስትርና የኢዜአ የቦርድ አባል ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ፤ ኢዜአ ትልቅ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ግንባታ ሥራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታና እውነታ መናገር፣ መስማትና ገጽታ መገንባት የሚችል የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ግንባታ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

የአገርን ገጽታ የሚገነቡ፣ የህዝብን ጥቅም የሚያስቀድሙና ብሄራዊ መግባባት ላይ ያተኮሩ ስራዎችን በጥራት መስራት እንዲችል ሪፎርም ሥራ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን ከፍ የሚያደርግ ሥራ እየሰራ መሆኑንም ነው ያመላከቱት።

እንደ ዶክተር ቢቂላ ገለጻ፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አማካኝነት የተሰጠው ሥልጠናም ”እንደ አገር እኛ አንድ ነን” የሚል መልእክት ያዘለ ነው።

ከ14 ተቋማት የተውጣጡ ሙያተኞች በአንድ ጣራ ሥር ሆነው በተመሳሳይ ርዕሶች ላይ ሲነጋገሩ እንደ አገር ያለው አጀንዳ አንድ መሆኑንም የሚያመለክት ነው ብለዋል።

በአሻባሪው ሕወሓት አማካኝነት የተከፈተውን ጦርነት መመከት የተቻለውም ኢትዮጵያዊያን በአንድነት በመነሳታቸው ነው ሲሉም እንደ ምሳሌ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው፤ ተቋሙ መሰል ሥልጠናዎችን እያሰፋ ይሄዳል ብለዋል።

ሥልጠናው እንደ አገር የአጀንዳ ቀረጻ ሥራ ምን ላይ ማተኮር እንዳለበትና ለዚህ የሚያግዙ ስልቶችን  አካቶ መሰጠቱንም አስታውሰዋል።

ስልጠናው በተግባር የተደገፈ መሆኑ ሰልጣኞች በቀጣይ በየተቋሞቻቸው የሚሰሯቸውን ስራዎች በብቃት መፈጸም እንዲችሉ ያግዛል ብለዋል።

ሰልጣኞቹም በቆይታቸው የተሻለ እውቀት ማግኘታቸውን ገልጸው፤ በቀጣይ በየተቋማቸው የተሻለ ሥራ ለመስራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ስልጠናው ከዚህ ቀደም በሚያውቋቸው ነገሮች ላይ ተጨማሪ እውቀት እንዲገበዩ እንዳደረጋቸውም ገልጸዋል።

ሥልጠናው ከታህሳስ 4 እስከ 15 ቀን 2014 ዓ.ም በጉዳዩ ላይ የተሻለ እውቀት ባላቸው ምሁራንና ሙያተኞች የተሰጠ ነበር።