ነጻ በወጡ የአማራ ክልል አብዛኛው አካባቢዎች ህዝባዊ አገልግሎት መስጠት ተጀምሯል

77

ባህርዳር፣ ታህሳስ 15/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ከአሸባሪው ህወሓት ነጻ በወጡ አካባቢዎች የፖለቲካ፣ የአስተዳደርና የጸጥታ መዋቅር በመዘርጋት ህዝባዊ አገልግሎት መሰጠት መጀመሩን በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ሀላፊ አቶ ሞላ መልካሙ ለኢዜአ እንደገለጹት መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች በወሰዱት እርምጃ የተወረሩ የክልሉ አካባቢዎች ከአሸባሪው ህወሃት ነጻ ወጥተዋል።

በየደረጃው ያሉ የክልሉ አመራሮችም ለመከላከያ፣ ለልዩ ሃይል፣ ለሚሊሻ፣ ለፋኖና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ድጋፍ በማድረግ ለተገኘው ድል አጋዥ ሚና መጫወታቸውንም አውስተው ከአሸባሪው ህወሀት ነጻ በወጡ 98 በመቶ አካባቢዎች የፖለቲካ፣ አስተዳደርና ጸጥታ መዋቅር በመዘርጋት  የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል።

በሰሜን ሸዋና ደቡብ ወሎ ወረዳዎች፣ በኮምበልቻና ደሴ ከተሞች፣ በሰሜን ወሎ ዞን፣ ኦሮሞና ዋግ ብሄረሰብ አስተዳደሮች የፖለቲካ፣ የአስተዳደርና የጸጥታ መዋቅሩን ወደ ስራ ማስገባት መቻሉንም ነው የተናገሩት።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የዘመቻ መሪነት ጠላት ከክልሉ ተጠራርጎ መውጣቱን ተከትሎ የክልሉ መንግስትና መሪ ድርጅት በስድስት ጉዳዮች ላይ በማተኮር ስራዎች መሰራታቸውን አስገንዝበዋል።

ከተከናወኑት ውስጥ የመንግስት መዋቅርን በፍጥነት በማስጀመር ህዝቡን በማረጋጋትና ከጦርነት ድባብ እንዲወጣ  በማድረግ ፈጥኖ ወደ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲገባ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

በአሸባሪ ቡድኑ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በአጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች የሚገኙ ዜጎችን ወደ አካባቢያቸው የመመለስና የጸጥታ ሀይሉን በሰው ሃይል ማጠናከር ሌሎች የተከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን አመልክተዋል።

"ጠላት የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን በማውደም አቅሙ የፈቀደለትን ጥፋት ሁሉ በመፈጸም ፀቡ እሱ እንደሚለው ከመንግስት ወይም ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ሳይሆን ከህዝብ ጋር መሆኑን በተግባር አረጋግጧል" ያሉት ሃላፊው ህዝብ እንዲማረር የማድረግ አላማ በመያዝ የመንግስት ተቋማትና የህብረተሰቡን አገልግሎት መስጫ ተቋማት በከፍተኛ ደረጃ አውድሞና ዘርፎ መሄዱን አመልክተዋል።

"የመብራት፣ የውሃና የቴሌኮም አገልግሎት መስጫ ተቋማትን፣ የንግድና የገቢ ማህደሮችንና ሌሎች የህዝብ ሰነዶችን በማጥፋት ማህበራዊ ቀውስ እንዲፈጠርና ህዝቡ እንዲያማርር አሳፋሪ ተግባር ፈጽሟል" ሲሉ  ነው ያስታወቁት።

በየደረጃው የሚደራጀው አመራርና ባለሙያ ችግሩን ለመቅረፍም ህዝቡን በቅንነት እንዲሁም በታማኝነት የማገልገልና ህዝባዊነትን የማስፈን ተግባራት እንዲያከናውን አቅጣጫ  ተቀምጦ ወደ ስራ መገባቱን  አቶ ሞላ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም