በአሸባሪው ሕወሓት ወረራ የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም የበኩላችንን እንወጣለን

67

ታህሳስ 15/2014/ኢዜአ/ በአሸባሪው ሕወሓት ወረራ የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋምና ወደ መደበኛ ህይወታቸው እንዲመለሱ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ።

አሸባሪው ሕወሓት በወረራ ይዞ በቆየባቸው በአማራና አፋር ክልሎች ንጹሃንን ገድሏል፤ ሴቶችን አስገድዶ ደፍሯል፤ የሕዝብና የግለሰብ ንብረቶችን አውድሟል።

ቡድኑ በሁለቱ ክልሎች የፈጸማቸውን ኢ ሰብዓዊ ድርጊት ተከትሎ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለው ለበርካታ ችግሮች ተጋልጠዋል።   

እነዚህን ዜጎች ወደ ቀያቸው ለመመለስና ወደ ቀድሞ መደበኛ ሕይወታቸው ለመመለስ መንግሥት በርካታ የመልሶ ማቋቋም ስራ እያከናወነ መሆኑ ይታወቃል።

መንግሥት የጀመረውም ዘርፈ ብዙ የመልሶ ማቋቋም ሥራ ግቡን እንዲመታ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወጣት ፋንታሁን ይዘዘው፤ ተፈናቃዮቹ ወደ ቀያቸው ተመልሰው መደበኛ ህይወታቸውን እንዲመሩ ለማድረግ የበኩሉን ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።   

መልዓከ ሰላም ቆሞስ አባ ዜና ማርቆስ ተርፎ የተፈናቀሉ ዜጎች መልሰው እንዲቋቋሙ ያልተቆጠበ ድጋፍ ማድረግ ይገባናል ብለዋል።

በችግር ላይ ያሉትን ወገኖች ለመርዳት ያላቸውን ቁርጠኝነትም አረጋግጠዋል።  

ሁሉም በሚችለው አቅም የተፈናቀሉ ዜጎችን ሊደግፍ ይገባል፤ ይህንን ማድረግ ከተቻለ የዜጎችን ችግር በፍጥነት ማቃለል ይቻላል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ መቅደስ ቦጋለ ናቸው።

የቀድሞ ጦር ሰራዊት አባል የሆኑት ስርገው አበበ፤ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋምና ለመርዳት ከእኔ ጀምሮ ኅብረተሰቡም ትብብሩን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በሁሉም የአገሪቱ አቅጣጫ የሚኖሩ ዜጎች ከቀያቸው ለተፈናቀሉና ለተቸገሩ ወገኖች የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም