በኢትዮጵያ በስርዓተ ትምህርት የታገዘ የሰላም ባህል ግንባታ ሊኖር ይገባል

105

አዲስ አበበባ ታህሳስ 15/2014(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም ለማስፈን በስርዓተ ትምህርት የታገዘ የሰላም ባህል ግንባታ ሊኖር እንደሚገባ ተመለከተ።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነት ላይ ምን ሊከናወን ይገባል በሚል ያዘጋጀው ምክክር ተካሂዷል።

በመድረኩም ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ እንዲሁም አሁናዊ ጉዳዮች ላይ የመወያያ ፅሁፎች ቀርበው ምክክር ተደርጎባቸዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላምና ደህንነት ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር ዮናስ ኤዳዬ፤ በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም ለማስፈን የመነጋጋር ባሀልን ማዳበር ይገባል።

ሠላም የፍትህና የልማት ጥያቄዎችን ጭምር የያዘ መሆኑን የሚገልጹት ዳይሬክተሩ ሰላም ሂደት በመሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ በሰላም ጉዳይ የነበሩ ክፍተቶችን በማረም የሠላም ባህል ግንባታ ላይ ማተኮር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ለዚህ ደግሞ የሰላምን ዋጋ ልጆች ከመዋዕለ ህጻናት ጀምሮ እንዲረዱት ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም በስርዓተ ትምህርት ውስጥ በማካተት ማስተማር ይገባል ብለዋል።

የሰላም ባህል ግንባታ ከእምነት ተቋማት አልፎ በትምህርት ቤቶች ሊስፋፋ ይገባል ለዚህ ደግሞ ተቋማቱ የድርሻቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ የተለያዩ ልዩነቶች ያለመግባባት ምክንያት ሊሆኑ አይገባም፤ ልዩነቶችን በተገቢው መንገድ በማስተናገድ ለሠላም መረጋገጥ መስራት እንደሚገባም ዶክተር ዮናስ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረማሪያም በበኩላቸው ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት በመሆኑ ሁላችንም የሰላማችን ባለቤቶች ሆነን መስራት አለበን ብለዋል።

የሰላም እጦት ምክንያት የሚሆኑ ነገሮች ሲያጋጥሙ በተከታታይ ውይይቶች እንዲፈቱ የማድረግ ልምዱ እንዲጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም