የምዕራባውያንን ያልተገባ ጫና በአሸናፊነት ለመወጣት የ"በቃ" ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል

59

እንጅባራ፤ ታህሳስ 15/2014 (ኢዜአ) የአንዳንድ ምዕራባውያን ያልተገባ ጫና በአሸናፊነት ለመወጣት የ"በቃ" ንቅናቄ ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ።

አንዳንድ ምዕራባውን አገራት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠርና በአፍሪካ ፍላጎታቸውን ለማሳካት የአሸባሪው ህወሓትን ኢ-ሰብኣዊ ድርጊትና ሀገር የማውደም ተግባር ከመቃወም ይልቅ ድጋፍ በመስጠት  ላይ እንደሚገኙ የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር መኮንን ዋሴ እንዳሉት፤አሜሪካን ጨምሮ  አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት በሰብአዊ መብት ሰበብ በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ጫናዎችን እያሳደሩ ነው።

ሚዲያዎቻቸውን ተጠቅመውም በሚነዙት የሐሰት መረጃ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በማሳሳት ቀጠናዊና አህጉራዊ ፍላጎታቸውን ለማስጠበቅ እየተሯሯጡ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ላይ ጫናው የቀጠለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅና እንደተፈለገ የማይጠመዘዝ አቋም ይዘው በመነሳታቸው እንደሆነም አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአፍሪካ ጭምር ራስን ስለመቻልና የጋራ ዕድገት መርህን ይዘው መነሳታቸው በምዕራባዊያኑ ዘንድ አልተፈለገም ያሉት ምሑሩ አፍሪካዊያን ተባብረው በጋራ እንዲለሙ፣ ከኢኮኖሚ ጥገኝነት እንዲላቀቁ እና በፀጥታው ምክር ቤት  አፍሪካ ድምጽ እንዲኖራት የተነሳው ጥያቄም ለምዕራባውያን ስጋት መሆኑን ገልጸዋል።

"የኢትዮጵያ ተሰሚነትና ተጽዕኖ ፈጣሪነት መጉላትና የአፍሪካ ሃብት ለአፍሪካዊያን የሚለው ድምጽ ከፍ ብሎ መደመጥ  የምዕራባውያን የእጅ አዙር ጭቆና እንዲያበቃ የሚያደርግ ነው" ብለዋል።

"አንዳንድ ምዕራባውያን ዛሬም አሸባሪውን ህወሓት እየደገፉ ያሉት ህወሓት ለኢትዮጵያ ህዝብ የተለየ ብልጽግና ስለሚያመጣ ሳይሆን ሀገሪቱን በበላይነት በመራባቸው ዓመታት እንዳሻቸው ሲጠመዝዙት ስለነበረና ይሄንን ፍላጎታቸውን አሁንም የማስቀጠል ጽኑ ፍላጎት ስላላቸው ነው" ሲሉም አስረድተዋል።

በሰብአዊ መብትና በዴሞክራሲ ሰበብ በኢትዮጵያ ሆነ በአፍሪካ ላይ  የሚያደርጉትን ያልተገባ ጫና በአሸናፊነት ለመወጣት የተጀመረው የ"በቃ" ንቅናቄ ዘመቻ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት።

አሸባሪው ህወሓትን የሚደግፉት ሀገራት ቡድኑ የሚፈጽመውን የጥፋት ድርጊት በመቃወም ፋንታ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ማሳደራቸው የኢትዮጵያንና የቀጠናውን ሀብት ሲመዘብሩ ስለመቆየታቸው አንድ ማሳያ እንደሆነ የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ዓለምነህ አጋጄ ናቸው።

እሳቸው እንደሚሉት "የውጭ ጫናው የቀጠለው ህወሓት በዘመኑ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ከመቆም ይልቅ ለአንዳንድ ምዕራባውያን ፍላጎት የሚመችና የሚታዘዝ መሆኑ፤ በአንጻሩ የአሁኑ የኢትዮጵያ መንግስት ለእነሱ የማይጠመዘዝ በመሆኑ ነው" ።

"ኢትዮጵያ አፍሪካውያንን በማስተባበር የውጭ ጫናውን ለዓለም ማህብረሰብ በማሳወቅ የጀመረችውን እንቅስቃሴ በማጠናከር ተፅዕኖውን ማስቆም ይገባል" ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህር ታደለ አምበሉ በበኩላቸው፤ "አንዳንድ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን መንግስትና ህዝብ በተፅዕኖ ስር ለማድረግ በመገናኛ አውታሮቻቸው ጭምር ዘምተዋል'' ብለዋል።

ምዕራባውያን የዴሞክራሲና የእውነተኛ መረጃ ምንጭ ተደርገው ሲወሰዱ የነበረ ቢሆንም በኢትዮጵያ ጉዳይ ባሰራጩት የፈጠራ ወሬ ተዓማኒነታቸው ጥያቄ ውስጥ መግባቱን ገልጸው "ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ውዥንብር ውስጥ በመክተት አሸባሪውን ወደ ስልጣን በማምጣት ያገኙ የነበረውን ጥቅም ዛሬም ለማስጠበቅ እያለሙ ሲሉ" ተናግረዋል።

"በሀገራችን ላይ የሚፈጸመውን ኢ-ፍትሐዊ ጫናና ጣልቃ ገብነትን በመከላከል ኢትዮጵያን ከሚደርስባት ጫና መታደግ የሁላችንንም ትብብር ይጠይቃል" ብለዋል።

እንደ መምህሩ ገለጻ ፤የአፍሪካ ሀገራት በምዕራባውያን ከሚደረግባቸው ጫና ለመላቀቅ የኢትዮጵያን አቋም ተቀብለው ማንጸባረቅ ያለባቸው ወቅት አሁን ነው።

ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በያሉበት የሚያደርጉትን የ"በቃ" ዘመቻ ዓለም አቀፍ ንቅናቄን አሁንም አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ነው ምሁሩ ያመለከቱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም