በኦሮሚያ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ጥምረት በኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ የውጭ ጣልቃ ገብነትና ጫናን አወገዘ

306

ሐረር፣ ታህሳስ 14 ቀን 2014 ( ኢዜአ) በኦሮሚያ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ጥምረት አሜሪካንን ጨምሮ አንዳንድ ምእራባዊያን ሀገራት የኢትዮዽያን ሉዓላዊነት በመጋፋት እያደረጉ ያለውን ጣልቃ ገብነትና ጫና አወገዘ።

በአፋርና አማራ ክልሎች ህወሀት ፈጽሞት በነበረው ወረራ የተጎዱ ወገኖችን በመደገፍና መልሶ በማቋቋም  ተግባር  ላይ በትኩረት እንደሚሰራም ጥምረቱ አመላክቷል።

ጥምረቱ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ባካሄደው ዓመታዊ ጉባዔ ላይ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ባለ ሰባት  ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ገመቹ አራርሳ የጥምረቱን የአቋም መግለጫ ይፋ አድርገዋል።

ጥምረቱ በአቋም መግለጫው አሜሪካንን ጨምሮ አንዳንድ ምእራባዊያን የኢትዮዽያን ሉዓላዊነት በመጋፋት፣ በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባትና ዘመናዊ ቅኝ ግዛትን መልሶ ለመዘርጋት የሚሸርቡትን ሴራ በመቃወም አውግዟል ።

በሰብዓዊ መብትና እርዳታ እንዲሁም የዜጎቻቸውን ደህንነት መጠበቅ በሚል ሰበብ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት በአሜሪካንና በሌሎች የምዕራብ ሀገሮች በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን አላስፈላጊ ጫናን እናወግዛለን ሲል ጥምረቱ በመግለጫው አስታውቋል።

በአንዳንድ የምእራባዊያን መገናኛ ብዙሀን፣ በግለሰቦችና ቡድኖች በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን ሚዛናዊነት የጎደለውና መሰረተ ቢስ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ከመንግስት፣ ከህዝቡና ከኢትዮዽያ ወዳጆች ጎን በመሆን ለመመከት እንደሚሰራ ጥምረቱ አመልክቷል።

ኢትዮጵያ ተገዳ የገባችበትን ጦርነት በድል በመቋጨትና ህዝቡ በተረጋጋ ሁኔታ ኑሮውን እንዲቀጥል ከመንግስትና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የሚጠበቅበትን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን በመግለጫው አስፍሯል።

በጦርነቱ ምክንያት የተጎዱ ወገኖችን በመርዳትና መልሶ በማቋቋም እንዲሁም በጦርነቱ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ በመገንባት የታቀዱ የልማት ስራዎች ለማስቀጠል አቅም በፈቀደ  ሁሉ ድጋፍ ለማበርከት እንደሚሰራ ጥምረቱ አስታውቋል ።

የአዳማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የጥምረቱ ሰብሳቢ ዶክተር ለሚ ጉታ በበኩላቸው አሸባሪው ህውሃት ጦርነት ከከፈተበት ጊዜ ጀምሮ የጥምረቱ አባል ዩኒቨርሲቲዎች ለሰራዊቱና በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች በገንዘብና በሌሎች ዘርፎች ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

ዶክተር ለሚ አክለው ጥምረቱ በቀጣይም በጦርነቱ የተጎዱትን በመደገፍና መልሶ በማቋቋም ስራ ላይ በገንዘብ፣ በዓይነትና በእውቀት ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

የህልውና ዘመቻው በድል ተጠናቆ አገሪቱ ሰላም እስክትሆን ለመከላከያና ሌሎች የጸጥታ ሀይሎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዶክተር ለሚ አስታውቀዋል ።

“ከውስጥና ከውጭ ሀይሎች በሀገር ላይ የተቃጣን ጥቃት ለመመከት ዩኒቨርሲቲዎች በሁሉም መድረኮችና አጋጣሚዎች የሀገሪቱን ትክክለኛ ገጽታና ሃሳብ በማንጸባረቅ የድርሻችንን መወጣት ይጠበቅብናል” ያሉት ደግሞ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል የሱፍ ናቸው።