ኮርፖሬሽኑ ለተፈናቃይ ወገኖች 15 ሚሊዮን ብር የሚገመት የዓይነት ድጋፍ አደረገ

69


ደብረ ብርሃን/ መተማ፤ታህሳስ 14/ 2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በአሸባሪው ህወሓት ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች 15 ሚሊዮን ብር የሚገመት የዓይነት ድጋፍ አደረገ።


የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ሰለሞን በድጋፍ ርክክብ ስነ ስርዓቱ ወቅት እንዳሉት፤ በአሸባሪው ህወሓት የጥፋት ተግባር ኢንዱስትሪ ፓርኮች ጉዳት ደርሶባቸዋል።

"ቡድኑ በአማራ ክልል በፈጸመው ወረራ በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ላይ ጉዳት በማድረስ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጫና በመፍጠር አፍራሽነቱን በተግባር አረጋግጧል" ብለዋል።

የጥፋት ቡድኑ በፈጸመው እኩይ ድርጊት በመቀሌ የሚገኘው የኢንዱስትሪ ፓርክ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እስካሁን ደረስ ምንም አለመታወቁንም ነው የጠቆሙት።

አሸባሪው ህወሓት የዜጎችን ህይወት በመቅጠፍ፣ ሀብትና ንብረታቸውን በማውደምና በመዝረፍ ከመኖሪያ ቀያቸው እንዲሰደዱ በማድረግ ግፍ መፈጸሙንም አውስተዋል።

ኮርፖሬሽኑ በአሸባሪው ቡድን ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን እና ሸዋሮቢት ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች 350 ኩንታል ዱቄት፣ 150 ኩንታል ስኳር፣ 7ሺህ 500 ሊትር ዘይት እና 1 ሺህ 500 ብርድ ልብስ ለግሷል።

የማብሰያ ቁሳቁስ፣ የሳሙናና የሴቶች ንጽህና መጠበቂያም እንዲሁ።

የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አበባው መለሰ በበኩላቸው፤ ለድጋፉ ምስጋና አቅርበው፣ በቀጣይም ተፈናቃይ ወገኖች እስኪቋቋሙ ድረስ ድጋፉ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

ኮርፖሬሽኑ ያደረገው ድጋፍ በአሸባሪው ቡድን ምክንያት ለችግር የተጋለጡትን ወገኖች መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት እንደሚያግዝ የገለጹት ደግሞ የሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ዘነበ ተክሌ ናቸው።

በተያያዘ ዜና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከ500 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የምግብ ድጋፍ ለምዕራብ ጎንደር ዞን የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ አስረክቧል።


ድጋፉን ዛሬ በገንዳ ውሃ ከተማ በመገኘት ያስረከቡት የዩኒቨርሲቲው የህዝብ ግንኙነት ባለሙያና የድጋፉ አስተባባሪ አቶ ምስጋናው ዓለሙ እንዳሉት፤ ከተደረገው ድጋፍ ውስጥ 13 ኩንታል ቴምር፣ 106 ኩንታል ኩኪስና ሌሎች የምግብ ዓይነቶች ይገኙበታል።


የምግብ ድጋፉ በዞኑ ሃብት አሰባሳቢ በኩል ለጸጥታው ሃይል የሚላክ መሆኑንም አመልክተዋል።


የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ያደረገው ድጋፍ ለጸጥታ ኃይሉ ተጨማሪ አቅምና ወኔ የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም