የዓመታዊው የቁልቢ ገብርኤል ንግስ በዓል ታዳሚዎችን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ዝግጅት ተደርጓል

101

ሐረር ፤ ታህሳስ 13 / 2014 (ኢዜአ) ለዓመታዊው የቁልቢ ገብርኤል ንግስ በዓል ወደ ስፍራው የሚጓዙ ምዕመናን እና ዲያስፖራዎችን ሰላምና ደህንነትን ለማስጠበቅ ዝግጅት መደረጉን ፖሊስ አስታወቀ።

የምስራቅ ሐረርጌ ዞኑ ፖሊስ መምሪያ የኮሙዩኒኬሽን ዲቪዥን ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ቶሎሳ ጉሹ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ታህሳስ 19  ለሚከበረው  የቁልቢ ገብርኤል  የንግስ በዓል ለመታደም  ምዕመናን፣ ቱሪስቶች፣አምባሳደሮች እና ዲያስፖራዎች እንደሚመጡ ይጠበቃል።

የእነዚህ ታዳሚዎችን  ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ አስፈላጊው  ዝግጅት  ተጠናቋል ብለዋል።

በዚህም የአጎራባች ዞን ፣ ክልልና የፌዴራል ጸጥታ አካላት በዓሉ ተከብሮ እስኪጠናቀቅ በሚሰሩ የሰላም ማስከበር ተግባራት ላይ በቁልቢ ገብርኤል ገዳም  ዛሬ  ውይይት ማካሄዳቸውን ተናግረዋል።

በውይይቱም ሁሉም የክብረ በዓሉ ታዳሚዎች  ወደ  አካባቢያቸው  በሰላም  እስኪመለሱ ድረስ የጸጥታ ሃይሉ የተቀናጀ ወንጀልን የመከላከል ስራ ለማከናወን ከምንጊዜውም በላይ ዝግጅት መደረጉን ዋና ኢንስፔክተር ቶሎሳ አስታውቀዋል፡፡

የበዓሉ ታዳሚዎች የግል ንብረቶቻቸውን እንዳይሰረቅ በጥንቃቄ በመያዝ ለጸጥታ ሃይሉ ድጋፍ እንዲያደርጉ አመልክተው፤ የንግስ በዓል በሚካሄድበት ስፍራ ሶስት ጊዜያዊ  ፖሊስ ጣቢያዎችና  ፍርድ ቤት መቋቋማቸውንም ጠቅሰዋል።

የበዓሉ ታዳሚዎች ወንጀል ፈጻሚዎችና የሚጠራጠሯቸውን እንዲሁም  ወድቆ የሚያገኙትን ንብረት ቁልቢ ገብርኤል አካባቢ ለሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ በአካል ወይም በስልክ ቁጥር 0256665650  ደውለው ማሳወቅ የሚችሉ  መሆኑን ዋና ኢኒስፔክተር ቶሎሳ ገልጸዋል።

በተጨማሪ በዘንድሮ በዓል የአካባቢውን ሰላም የበለጠ አስተማማኝ ለማድረግ በገዳሙ ዙርያ ምንም ዓይነት ግብይት እንደማይከናወን አስታውቀዋል።

የትራፊክ አደጋን ለመከላከል በዓሉ የሚከበርበት ቦታ ለተሽከርካሪ አስቸጋሪ  በመሆኑ አሽከርካሪዎች የትራፊክ ህግና ደንብን አክብረው በማሽከርከር በሰው ህይወትና ንብረት ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመታደግ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ከታህሳስ  17 ቀን 2014 ዓ.ም  ጠዋቱ 12 ሰዓት   ጀምሮ እስከ ታህሳስ 19 ቀን 2014 ዓ.ም  ምሽት 12 ሰዓት ድረስ ከጨለንቆ እስከ ቀርሳ ከተማ ባለው ዋና መንገድ ላይ ከባድ ተሽከርካሪ ማለፍ ሆነ  ማቆም የተከለከለ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም