በመንግስት ላይ ጫና በመፍጠር የአሸባሪውን ህወሃት እድሜ ለማራዘም የሚጥሩ አካላት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በደል እየፈፀሙ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል

70

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 13/2014 (ኢዜአ) በመንግስት ላይ ጫና በመፍጠር የአሸባሪውን ህወሃት እድሜ ለማራዘም የሚጥሩ አካላት በኢትዮጵያ ህዘብ ላይ በደል እየፈፀሙ መሆኑን ሊገነዘቡ እንደሚገባ በደቡብ አፍሪካ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባል የሆኑት አቶ በኃይሉ መሀመድ ተናገሩ።

አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን ለማፍረስ በሚል በከፈተው ጦርነት በተለይም በአማራ እና አፋር ክልሎች ያልፈፀመው እኩይ ድርጊት የለም።

የሽብር ቡድኑ የህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን እያደነ በመዝረፍና በማውደም ህዝብ የማህበራዊ ቀውስና ችግር ላይ እንዲወድቅ አድርጓል።

በወረራ ገብቶባቸው በነበሩ አካባቢዎች ሁሉ ሰላማዊ ሰዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ከመግደል በተጨማሪ ከህፃናት እስከ አረጋዊያን በመድፈር የጭካኔውን ልክ አሳይቷል።

በደቡብ አፍሪካ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባልና የዩናይትድ ሚዲያ ሃውስ መስራች አቶ በኃይሉ መሀመድ፤ በመንግስት ላይ ጫና በመፍጠር የአሸባሪውን ህወሃት እድሜ ለማራዘም የሚጥሩ አካላት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በደል እየፈፀሙ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል ብለዋል።

አሸባሪው ህወሃት ከኋላ ''አይዞህ'' በሚሉት የእጅ አዙር የቅኝ ገዥዎች እየተመራ በአገርና ህዝብ ላይ ይቅር ሊባል የማይችል ወንጀል መፈፀሙን ጠቅሰዋል።

ቡድኑ የግል ጥቅሙን ከሀገርና ህዝብ ህልውና በማስበለጥ ከኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች ጋር አገር የመበታተን የጥፋት ግንባር በመፍጠር እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና በመፍጠር የአሸባሪውን ህወሃት እድሜ ለማራዘም የሚጥሩ አካላት ሁሉ በህዘብ ላይ የከፋ በደል እየፈፀሙ መሆኑን በቅጡ ሊገነዘቡ ይገባል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የገጠማትን ወቅታዊ ፈተና ተቋቁማ በአሸናፊነት የመወጣት አቅምና ችሎታው ያላት መሆኑን ጠቅሰው በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ገብተው ጫና የሚያሳድሩ አገራትም ከድርጊታቸው መታቀብ አለባቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያን ወቅታዊ ጉዳይ በመረዳት በርካታ ምሁራን በጋራ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አንስተው ጅምሩ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው መልካም ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ፍፁም ሰላምና መረጋጋት የሌለ በማስመሰል የሀሰት መረጃ የሚያሰራጩ ሚዲያዎችም ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም