የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች ተፈናቃይ ዜጎችን ለማቋቋም ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ያደርጋሉ

199

ሚዛን አማን፤ ታህሳስ 13/2014 (ኢዜአ) የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች በአሸባሪው ህወሓት ጥቃት የደረሰባቸውን የአማራና የአፋር ክልል ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታወቁ።

ነዋሪዎቹ ለኢዜአ እንደገለጹት በአሸባሪው ህወሓት ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉና ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በሚችሉት አቅም መልሶ ለማቋቋም ዝግጁ ናቸው።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ዘሪሁን በየነ እንዳሉት ከጥንት ጀምሮ የዳበረውን የመረዳዳት ባህል በማጎልበት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በሚችሉት ሁሉ ከጎናቸው በመሆን ወደ ነበሩበት ሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱ እናደርጋለን ብለዋል።

ጠንክረን ከሰራንና ከተሳሰብን በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት የደረሰባቸውን የአማራና አፋር አካባቢዎችን መልሶ መገንባትና ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ማቋቋም የማይቻልበት ምክንያት እንደሌለም ተናግረዋል።

የተራቡትን ማብላት፣ የታረዙትን ማልበስ እንዲሁም ማረፊያ ላጡት መጠለያ መስራት በሁሉም እምነት የሚታዘዝና የሞራል ግዴታ መሆኑን ጠቁመዋል።

“ሁሉም ነገር በእጃችን ነው እጅ ለእጅ ተያይዘን ኢትዮጵያን እናለማለን” ያሉት ደግሞ የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪ አቶ ኤልያስ ሽባባው ናቸው።

የሚጠበቅባቸው ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው፤ ኢትዮጵያዊያን የወገኖችን ችግር በማስቀደም በአሸባሪው ህወሓት የተጎዱ ወገኖቻችንን ለማቋቋም መዘጋጀት አለብን ብለዋል።

የወደሙ መሠረተ ልማቶችን ለመጠገንና እንደ አዲስ የሚሰሩትን ለመስራት መንግሥት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ እንደ ዜጋ የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም አስታውቀዋል።

”ለተጎዱ ወገኖቻችንና ለሀገራችን ከእኛ በተሻለ የሚጨነቅና የሚረዳ አካል ሊኖር አይችልም” ያሉት አቶ ኤልያስ በዚህ ወቅት ወገንን መርዳት የፍላጎት ብቻ ሳይሆን ሞራልና ኢትዮጵያዊነት የሚያስገድደው ጉዳይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያን ለማዳከምና ለማፍረስ ታስቦ በአሸባሪው ህወሓት በአማራና አፋር ክልሎች በተፈጸሙ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ከፍተኛ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት ደርሷል ያሉት ደግሞ አቶ ጌትነት መንገሻ ናቸው።

በመሆኑም ሁላችንም ከተረፈን ሳይሆን ካለን አካፍለን እየሰጠን ወደ ቀድሞ ህይወታቸው እንዲመለሱ  ከተጎዱ ወገኖች ጎን ሆነን ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ዮናስ ኬና ተጎጂዎችን መልሶ ማቋቋም ቀዳሚ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ የመልሶ ማቋቋም ስራን በተቀናጀ መልኩ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የዞኑ ኅብረተሰብ እስካሁን ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉንም አክለው ገልጸዋል።