የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ከጭልጋ ወረዳ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረገ

98

ጎንደር (ኢዜአ) ታህሳስ 13/2014---የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በጭልጋና አካባቢው በሰው ሰራሽ አደጋ ሳቢያ ለተፈናቀሉና ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው ለ1ሺ 440 ነዋሪዎች የአልሚ ምግብ ድጋፍ አደረገ።

ማህበሩ ድጋፉን ያደረገው ኢንተርናሽናል ክሊኒካል ላቦራቶሪ ከተባለ ሀገር በቀል የጤና ተቋም ባገኘው የ700 ሺህ ብር ድጋፍ መሆኑን በማህበሩ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ አስተባባሪ አቶ ሻምበል ዋላ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

ድጋፉ የተደረገላቸው ከጭልጋ ወረዳና አካባቢው ተፈናቅለው በአይከል ከተማና በጫንድባ ቀበሌ በጊዜያዊ መጠለያና በዘመድ ተጠግተው የሚገኙ 1 ሺህ 440 እናቶችና ህጻናት ሲሆኑ ድጋፉም 153 ኩንታል ፋፋ እና ብስኩት መሆኑን አቶ ሻምበል ተናግረዋል፡፡

ማህበሩ በሌላም በኩል በአማራ ክልል በሽብር ቡድኑ ወረራ ሳቢያ ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸውና ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሰብአዊ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ማህበሩ ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ በኮምቦልቻ፣ በደሴ ፣በዳባት፣ በደባርቅ፣ በደብረብርሃን፣ በገረገራ፣ በእብናትና ፍላቂት አካባቢዎች ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ አድርጓል፡፡

ሰብዓዊ ድጋፉ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶችን ያከተተ ሲሆን በዚህም ከ280 ሺህ በላይ ወገኖችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ማህበሩ በቀጣይ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ ሻምበል አረጋግጠዋል።

የኢንተርናሽናል ክሊኒካል ላቦራቶሪ የጤና ተቋም ተወካይ አቶ ከሁሉም በላይነህበበኩላቸው ድጋፉ የተቋሙ ሠራተኞች ከወር ደመወዛቸው በመቀነስ የለገሱት መሆኑን ተናግረዋል፡፡  

በዚህም ዋጋው 700 ሺህ ብር የሆነ 153 ኩንታል የአልሚ ምግብ ለተፈናቀሉ ወገኖች መለገሱን ገልጸዋል።

ተቋሙ የሽብር ቡድኑ በከፈተው ጦርነት የወደሙ የጤና ተቋማትን ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ላቦራቶሪዎችን በቁሳቁስ የማጠናከር ቀጣይ ዓላማ እንዳለውም አመልክተዋል።

ድጋፉ ከተደረገላቸው እናቶች መካካል ወይዘሮ ማሪቱ መኳንንት እና ወይዘሮ አማረች ሲሳይ፥ ድጋፉ የዕለት ችግራቸውን ለማቃለል እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ ወደአካባቢያቸው ተመልሰው የተረጋጋ ኑሮ ለመምራት መንግስት ዘላቂ ድጋፍ እንዲደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም