ጅማ እንግዶቿን ለመቀበል እየተዘጋጀች ነው

259

ጅማ ፤ታህሳስ 13/2014 (ኢዜአ) ወደ ታሪካዊቷ ጅማ ከተማ የሚመጡ የውጭ እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የከተማዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

አንዳንድ የምዕራባዊያን ሀገራትና  መገናኛ ብዙሃኖቻቸው በኢትዮጵያ ላይ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ የሚነዙትን ለመቀልበስና ሀገሪቷን መልካም ገጽታዋን ለዓለም ታሳይ ዘንድ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያን ለገና በዓል ወደ ሀገር ቤት እንዲመጡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

አንድ ሚሊዮን እንግዶች እንደሚመጡ በሚጠበቀው በዚሁ ጊዜም በተለይም ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የቱሪዝም ስፍራዎችን  መጎብኘትና ማልማት የሚፈልጉ እንግዶችን በኢትዮጵያዊው መልካም መስተንግዶ መቀበል ያስፈልጋል።

ከዚህ አንጻር በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የምትገኘው ታሪካዊቷ የጅማ ከተማ በቆየው የእንግዶች አቀባበል ባህሏ ለዚህ ታሪካዊው ጊዜ እየተዘጋጀች ትገኛለች።

የከተማዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት  የታሪክ ባለሙያና የሙዚየም ሃላፊ አቶ ነጁብ ራያ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ዝግጅቱ እንግዶች ለበዓሉ ሲመጡ ወደ ጅማም ጎራ ብለው  ታሪካዊ ቦታዎችን እንዲጎበኙና በቆየታቸው ጥሩ ጊዜ አሳልፈው ሊሳተፉበት  የሚፈልጉትን  የልማት አማራጮችንም  እንዲዳስሱ ለማስቻል ጭምር ነው።

ጅማ ከምትታወቅባቸው ቦታዎች ትልቁ የአባ ጅፋር ቤተ መንግስት ዋነኛው የቱሪዝም መስህብ ነው ይላሉ።

ታሪካዊው የጅማ ሙዚየም፣ አዌቱ መናፈሻና  ሌሎች ቦታዎችን ለመጎብኘት ያሰቡ እንግዶች በትራንስፖርት እንዳይቸገሩ የከተማ አስተዳደሩ ሰርቪሶች ነጻ አገልግሎት ለመስጠት ተመቻችቷል ብለዋል።

ከማረፊያ ሆቴሎች ባለቤቶች ጋር በመነጋገርም ለእንግዶቹ የተመቻቸ ሁኔታን በመፍጠር የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተሰናዱ መሆናቸውን አቶ ነጂብ ገልጸዋል።

ታሪካዊ ቦታዎቹን የማጽዳት፣ የሚጎበኙ የተፈጥሮ መስህቦችን ዝግጁ የማድረግና ተያያዥ የከተማ ጉዳዮችም በመከናወን ላይ አንደሚገኘ አመላክተዋል።

የጅማ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የኮሙዩኒኬሽን ዲቪዥን ሃላፊ ዋና ኢንፔክተር ገዛኸኝ አውግቸው በበኩላቸው፤ በጸጥታው በኩል አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ በመሆኑ እንግዶች ያለምንም ስጋት ወደ ከተማዋ መጥተው ጥሩ ማሳለፍ እንደሚችሉ አስታውቀዋል።

ጅማ  ሰላማዊ ከተማ  መሆኗን የገለጹት ዋና ኢንስፔክተሩ፤ ህብረተሰቡና ፖሊስ በቅንጅት በመስራት የነበረ ሰላሟን ለማስቀጠል  ተግተን እንሰራለን" ብለዋል።

በከተማው የሴንትራል ሆቴል ማናጀር አቶ ኩምሳ ከበደ በሰጡት አስተያየት፤ ከውጭ የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ ሆቴሉ ከሁሉም አገልግሎቶች የ30 በመቶ ቅናሽ አድርጓል ብለዋል።

የምግብ፣ የመጠጥ፣ የመስተንግዶና የመዝናኛ አገልግሎቶች ተሟልተው እንግዶችን ለመቀበል መዘጋጀታቸውን ነው የገለጹት።

ጸጥታ የሰፈነበት ንጹህ የመኝታና የምግብ አገልግሎት በተሟላ ሁኔታ ለመስጠት ዝግጅት ማድረጋቸውን የተናገሩት ደግሞ የኤባ ሆቴል ባለቤት አቶ ናስር አብዶ ናቸው።

በአስተማማኝ መስተንግዶና አገልግሎት  እንግዶችን  ለመቀበል እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ነው አስተያየት ሰጪው ያስታወቁት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም