ሀገራዊ የምክክር መድረኩ የሀገረ-መንግስት ግንባታ እንጂ ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር የሚደረግ ድርድር እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል

75

ታህሳስ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሀገራዊ የምክክር መድረኩ በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች እና ሀገረ-መንግስት ግንባታ እንጂ ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር የሚደረግ ድርድር እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት በተለያዩ ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ እንዳሉት በቀጣይ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በዋናዋና አገራዊ ጉዳዮችና ሀገረ-መንግስት ግንባታ ላይ ትኩረት ያደረገ አገራዊ የምክክር መድረክ ይካሄዳል፡፡

አገራዊ የምክክር መድረኩ ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር የሚደረግ ድርድር አለመሆኑንም ገልፀዋል::

ሚኒስትር ዴኤታው በመግለጫቸው አገራዊ የምክክር መድረኩ ሪፎርም ከተጀመረ ወዲህ ዘላቂ የሠላም ግንባታ ለማምጣት የታሰበ ነው።

በአሁን ወቅት አንዳንድ ግለሰቦች ጉዳዩን በደንብ ባለመረዳታቸው ከአሸባሪው ቡድን ጋር የሚደረግ ድርድር አድርገው ማሰባቸው ስህተት እንደሆነ ተናግረዋል።

አገራዊ የምክክር መድረኩ ሁሉን አካታች የሆነ ሠላምና አገረ መንግስት ግንባታ ላይ ያተኩረ እንደሆነና ለዚህም ነጻና ገለልተኛ ተቋም ለመመስረት በሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

መድረኩ እንዴትና በምን አይነት ሁኔታ እንደሚካሄድ የራሱ መመሪያ ተዘጋጅቶለት በነጻና ገለልተኛ ተቋም እንደሚመራም ጠቅሰዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም አንዳንድ የውጭ ሀገራት ሚዲያዎች አሸባሪው የህወሃት ቡድን ለሰላም ብሎ ስልታዊ ማፈግፈግ አድርጓል በሚል አሁንም ህወሓትን ለማዳን የተለመደ የውሸት ዘገባቸው ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል::

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም