የትግራይ እናቶች "ልጆቻችን የት ናቸው" በማለት አሸባሪውን ቡድን መጠየቅ አለባቸው

115

ታህሳስ 13/2014/ኢዜአ/ የትግራይ እናቶች ልጆቻቸው የት እንዳሉ አሸባሪውን የህወሓት ቡድን መጠየቅ እንዳለባቸው አስተያየታቸውን የሰጡ የትግራይ ተወላጆች ተናገሩ፡፡

አሸባሪው ቡድን በአማራ እና በአፋር ክልሎች የትግራይን ሕዝብ አንገት ያስደፋ አረመኔያዊ እና ኢ-ሠብዓዊ ተግባራትን መፈጸሙንም ገልጸዋል፡፡

የትግራይ ሕዝብ ለዘመናት አብሮ ከኖረው ወንድሞቹ ጋር ያለውን ጥሩ የኑሮ መስተጋብር ለማቋረጥ በማሰብ አሸባሪው ቡድን በአጎራባች ክልሎች ግፍ መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡

ቡድኑ በወረራ ይዟቸው በነበሩ የአማራ እና የአፋር አካባቢዎች ዕድሜ ሳይለይ ከህጻን እስከ አዛውንት መጨፍጨፉን፣ በጦርነቱ ውስጥ ያልተሳተፉ ንጹሃንን መግደሉንም ገልጸዋል፡፡  

አሸባሪው ቡድን ከጥንትም የተካነበትን ሕዝቦችን የመለያየት ሴራ አሁንም በመጠቀም እታገልለታለሁ የሚለውን ሕዝብ ጭምር አንገቱን በማስደፋት ታሪክ ይቅር የማይለው በደል መፈጸሙንም አስረድተዋል።

የትግራይን ሕዝብ ከኢትዮጵያ ለመለየት እያሴረ የሚገኘው የህወሓት የሽብር ቡድን ሴራው መቼም ቢሆን የማይሳካ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ በአማራና በአፋር ክልሎች ግፍ የፈጸመባቸውን ሁሉ ከጎናቸው ሆነን ልናጽናናቸው ይገባልም ሲሉ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

በዚህም ሁሉም የትግራይ ተወላጅ አሸባሪውን ህወሓት ከማውገዝ እና ለሱ ተባባሪ ካለመሆን ጎን ለጎን ንብረታቸው ለወደመባቸው ወገኖች ድጋፍ በማድረግ አገራዊ ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡    

የሰላም አምባሳደር ምዑዝ ገብረህይወት በሰጡት አስተያየት በአማራ እና አፋር ክልሎች የተፈፀመው ግፍ ማዘናቸውን ገልፀው "ድርጊቱ ቤተሰብ የሆንን፣ የተዋለድን የተጋመድን፣ አብረን የኖርን አንድ ባህል ያለን ሰዎች ላይ የተፈፀመ በመሆኑ እንቅልፍ የሚነሳ ነው" ብለዋል፡፡

አቶ ናትናኤል ብርሃነ በበኩላቸው አሸባሪው ህወሃት ደፋ ቀና እያለ የሚሰራውን ሕዝብ፣ ህጻኑን፣ ወጣቱን፣ ሸማግሌውን፣ አሮጊቱን ሳይባል መጨፍጨፉ  የትግራይን ሕዝብ አንገት ያስደፋ ተግባር  መሆኑን ገልፀዋል፡፡

This image has an empty alt attribute; its file name is image-12.png

"ወገናችን በሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት አንገት እንድንደፋ አስደርገውናል፡፡" ሲሉ አክለዋል፡፡  

ወይዘሪት ብስራት ሃይሌ በበኩሏ  የተፈፀመውን ግፍ የትግራይ ተወላጅ የሆነ ሁሉ ማውገዝ እንዳለበት ጠቅሳ "የትግራይ ወጣት በብርም ፣ በጉልበትም ማገዝና መከላከያውንም መደገፍ ይጠበቅብናል፡፡" ብላለች

የትግራይ ሕዝብ በአሸባሪው ቡድን አፈና ውስጥ ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ  ከዚህ ለመውጣት ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ቡድኑን ለማጥፋት የሚደረገውን እንቅስቃሴ መደገፍም ይገባል ብለዋል።

ይህም ብቻ አይደለም የትግራይ እናት በአሸባሪው ቡድን የተነጠቀችው ልጇ የት እንዳለ መጠየቅ አለባት ብለዋል አስተያየት ሰጪዎቹ።

የትግራይ ወጣቶችም ከአሻባሪው ቡድን ጋር ባለመተባበር መሣሪያቸውን በማስቀመጥ እጃቸውን ለመከላከያ ሠራዊቱ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የትግራይ ሕዝብ ከአሸባሪው ቡድን ጋር ተባባሪ ባለመሆን እየፈጸማቸው ከሚገኙ ግፎች በቃህ ሊለው እንደሚገባም አመልክተዋል።

አቶ ናትናኤል ብርሃነ በሰጠት አስተያየት "እናቶች የት አሉ ልጆቼ ይበሉ፣ ያተረፍኩት ሞትን፣  ድህነትን ረሃብን ነው ብለው ሊጠይቁ ይገባል፡፡ ልጆችም ራሳቸውን አገራቸውን ማስከበር መቻል አለባቸው፡፡ እዚህ ያለውም የትግራይ ማኅበረሰብ አንድ ሆኖ ተደራጅቶ ይህንን ህገወጥ የሆነ ፓርቲና ሽብርተኛ ሊቃወም ይገባል፡፡"   

ወይዘሪት ብስራት ሃይሌ በበኩሏ  " እናቶች ከዚህ በኋላ ልጆቻቸውን አይላኩ፣ የላኩም ልጄ የት አለ ብለው  መጠየቅ አለባቸው፡፡ ምክንያቱም የሚንከባለለው እሳት ላይ ነው፡፡ ውጪ ያሉት መሬት ላይ ነው የሚንከባለሉት እነዚህ ግን እሳት ላይ ነው፣ እሳት ላይ መቀለድ አይቻልም፡፡ ልጆቹም የገቡት ተደገው ሊሆን ይችላል ምክንያቱም የትግራይ ሕዝብ ተጨቁኖ ነው ያለው፡፡ ወይ ልጅሽን ስጪ ወይ ትገደያለሽ ፡፡ ስለዚህ አንዴ የወጡትም እጃቸውን ለመከላከያ ይስጡ፡፡"ብላለች፡፡

የሰላም አምባሳደር ምዑዝ ገብረህይወት  አሸባሪው ህወሓት እየተዋጋ ያለው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር መሆኑን ጠቅሰው  ወጣቶች መሳሪያቸውን አስቀምጠው ለመንግስት እጃቸውን እንዲሰጡና  አባቶችና እናቶች ከቻላችሁ ልጆቻችሁን ወደ ጦርነት አትላኩ ብለዋል፡፡

የትግራይ ሕዝብ አሸባሪውን ቡድን ወደ ሕግ ለማቅረብ በሚደረገወ ሂደት የራሱን አስተዋጽኦ በማድረግ ታሪካዊ ሃላፊነቱን መወጣት እንዳለበትም አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም