አንዳንድ አገራት ዓለም አቀፍ ተቋማትን እንደ ፖለቲካ መሳሪያ በመጠቀም እየተቀበረ ያለውን አሸባሪው ሕወሓትን ለማዳን እየሞከሩ ነው

56

ታህሳስ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ)አንዳንድ አገራት ዓለም አቀፍ ተቋማትን እንደ ፖለቲካ መሳሪያ በመጠቀም እየተቀበረ ያለውን አሸባሪው ሕወሓትን ለማዳን እየሞከሩ መሆኑን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟንና ሉዓላዊነቷን የሚጋፉ የትኛውንም አይነት ድርጊቶችን እንደማትቀበልም ገልጿል።

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ በዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

‘በዘመቻ ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት” ባለፈው ሶስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ የአገር መከላከያ ሰራዊትን ጨምሮ ሌሎች የጸጥታ አካላት በአሸባሪው ሕወሓት ላይ በወሰዱት የተጠናከረ ኦፕሬሽን አሸባሪው ሕወሓት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ መድረሱን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ ወደ አማራና አፋር ክልሎች ካስገባው ሃይል አብዛኛው መደምሰሱንና ክልሎቹም ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ነጻ ወጥተዋል ብለዋል።

ይሁንና አሸባሪው ቡድን ሽንፈቱን ላለመቀበል ከአማራና አፋር ክልሎች የወጣሁት ለሰላም ነው ሲል የሀሰት ትርክቱን እየገለጸ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ይህ የአሸባሪው ሕወሓት ትርክት የትግራይን ሕዝብ የማታለልና ለዳግም ጦርነት ለመማገድ እየተጠቀመበት ያለው ስልት እንደሆነ ነው አቶ ከበደ ያስረዱት።

አንዳንድ አገራትም የሽብር ቡድኑ ፕሮፓጋንዳ ተቀብለው ቡድኑ የወጣው ለሰላምና ለዲፕሎማሲ እድል ለመስጠት በማለት እያራገቡት ይገኛሉ ብለዋል።

አገራቱም ከሰሞኑ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤትና የድርጅቱ የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ስብስባ ላይ ያንጸባረቁት አቋም እየተቀበረ ያለውን አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ለማዳን እያደረጉ ያለውን ጥረት የሚያሳይ እንደሆነ ገልጸዋል።

የጸጥታው ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ ያደረገው ስብስባ “ያለ ስምምነትና ውሳኔ ተበትኗል” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ወዳጅ አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን ያልተገባ ጫናና ውሳኔ አንቀበልም በማለት ተቃውሞ ማሰማታቸውን ተናግረዋል።

የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤትም በኢትዮጵያ ላይ ያሳላፈውን የውሳኔ ሀሳብ ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው ማሳወቋንም አስታውሰዋል።

አንዳንድ አገራት ዓለም አቀፍ ተቋማትን እንደ ፖለቲካ መሳሪያ በመጠቀም እያደረጉት ያለው ያልተገባ ጫና ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አካል ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟንና ሉዓላዊነቷን የሚጋፉ የትኛውም አይነት ድርጊቶችን እንደማትቀበልም ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያስገነዘቡት።

መንግስት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ድጋፋቸውን እያሳዩ ላሉ አገራት ምስጋናውን ያቀርባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም