በመዲናዋ በከተማ ግብርና ለተሰማሩ አርሶአደሮች የገበያ ትስስር በመፍጠር የኑሮ ወድነትን ለማቃለል እየተሰራ ነው

52

ታህሳስ 13/2014/ኢዜአ/ በመዲናዋ በከተማ ግብርና ለተሰማሩ አርሶአደሮች የገበያ ትስስር በመፍጠር የኑሮ ወድነትን ለማቃለል እየተሰራ መሆኑን የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ገልጿል፡፡

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ መሃመድ ሊጋሊ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በመዲናዋ በከተማ ግብርና ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮችን ከሸማቾች ጋር በቀጥታ በማገናኘት ግብይት የሚፈጽሙበት አሰራር ተዘርግቷል፡፡

አርሶ አደሩ ያመረተውን ምርት በቀጥታ ለሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር እንዲያስረክብና ሸማች ህብረት ስራ ማህበራት በበኩላቸው በተመጣጣኝ ዋጋ ለነዋሪው እንዲያቀርቡ የሚያስችል ትስስር መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ለአዲስ አበባ የምግብ ፍጆታ የሚውሉ ምርቶች ተደራሽነት እንዲጨምር ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

የከተማ አስተዳድሩ ከአራት ዓመታት ወዲህ ለአርሶ አደሩ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን እያቀረበ መሆኑን ገልጸው፤ በ2013 ዓ.ም ብቻ 20 ሺ ኩንታል ማዳበሪያ በመግዛት ለአርሶ አደሩ ማሰራጨቱን ለአብነት አንስተዋል፡፡

ለዚህ ይረዳ ዘንድ አርሶ አደሮቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ እንዲገቡ በጀት መመደቡንም ተናግረዋል።

በተጨማሪ አርሶ አደሩ የተሻለ ምርት በማምረት በከተማዋ ከምግብ ፍጆታ ጋር በተያያዘ የሚታየውን እጥረት እንዲፈታ ለማድረግ የምርጥ ዘርና የእርሻ ትራክተር የማቅረብ ስራ መከናወኑንም ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

የግብርና ስራውን በምርምር መደገፍም እንዲሁ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም