የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ለመከላከያ ሠራዊት እና ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

180

ታህሳስ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ለአገር መከላከያ ሠራዊት እና ለተፈናቀሉ ወገኖች 13 ሚሊዮን 100 ሺህ ብር የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ አደረገ።

ከከተማ አስተዳደሩ ገቢዎች ቢሮ በተጨማሪ እየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት፣ የበልስቲ ነጋሳና ልጆቹ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ ድርጅት እንዲሁም ሄቨን ኤምባሲ ቤተክርስቲያን የተሰኘ ተቋም በድምሩ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል።

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ሙሉጌታ ተሰራ፤ ቢሮው ያደረገው ድጋፍ ከ6 ሺህ በላይ የቢሮው ሠራተኞች የተሰበሰበ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሀገራችን የገጠማትን ፈተና በጋራ ሆነን እንወጣዋለን ያሉት ኃላፊው፤ ሠራተኞቹ በተነሳሽነት ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበው ድጋፉ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ደመረ ጸሐይ ለመከላከያ ሠራዊቱ እና በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድርጅቱ የ1 ሚሊዮን 200 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

የድርጅቱ ሠራተኞችም ከ70 ሺህ ብር በላይ እገዛ ማድረጋቸውንና በቀጣይም የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል።

የበልስቲ ነጋሳና ልጆቹ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ሥራ አስኪያጅና ባለቤት አቶ መዝገቡ በልስቲ በበኩላቸው በትናንትናው እለት በአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ በመገኘት 1 ሚሊዮን ብር  በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸው፤ ዛሬ ደግሞ የ1 ሚሊዮን 100 ሺህ ብር የአይነት ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡

ድጋፉን የተረከቡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ድጋፉን ላደረጉ ተቋማትና ድርጅቶች ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም ይህ አይነቱ የነቃ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ለመከላከያ ሠራዊትና የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማቋቋም ለሚያደርገው እንቅስቃሴ የከተማዋ ነዋሪ የሚሰጠው ምላሽ ከፍተኛ መሆኑን በማስታወስ፤ ይህ ህብረት አገራችንን ወደ ምትፈልገው የእድገት ጎዳና ሊያደርሳት የሚችል ነው ብለዋል፡፡

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።