በኢትዮጵያ ሃይቆች ላይ እየተሰፋፋ ያለውን የእምቦጭ አረም ለመከላከል በዋናነት በአረሙ አደገኝነት ላይ የጋራ ግንዛቤ መያዝ ያስፈልጋል

85

አዲስ አበባ፣  ታህሳስ 12/2014(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ሃይቆች ላይ እየተሰፋፋ ያለውን የእምቦጭ አረም ለመከላከል በዋናነት በአረሙ አደገኝነት ላይ የጋራ ግንዛቤ መያዝ ያስፈልጋል ሲሉ አረሙን በሚመለከት ምርምር የሰሩት የ3ኛ ዲግሪ ተማሪ ዳንኤል ወልደሚካኤል ተናገሩ። 

የእምቦጭ አረም  በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚራባና ሰፊ ቦታ የሚያዳርስ የውሃ ውስጥ አረም ነው።

አረሙን በሚመለከት ምርምር የሰሩትና በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪ የሆኑት ዳንኤል ወልደሚካኤል እንደሚሉት፤ የእምቦጭ አረም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከታወቁ አራት አደገኛ ወራሪ አረሞች መካከል አንዱ ነው፡፡

የመስፋፋት ሂደቱ በጣም ከፍተኛ የሆነው ይህ አረም፤ በኢትዮጵያ የውሃ ሃብት ላይ አደጋ መደቀኑን አስታውቀዋል።

አረሙን በተመለከተ ባደረጉት ጥናትም እምቦጭ የውሃ ትነትን በ7 እጥፍ እንደሚጨምርና ይህም በሂደት የውሃ አካላትን እንደሚያደርቅ ማረጋገጣቸውን አስረድተዋል።

አረሙ ወደ ውሃ አካላት ውስጥ ከገባና መሬት ከያዘ በኋላ ለመከላከል ከባድ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም አረሙን ለመከላከል የመጀመሪያው ተግባር ወደ ሃይቆች እንዳይገባ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ህብረተሰቡ በአረሙ አደገኝነት ላይ የጋራ ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል ነው ያሉት፡፡

በተለይ ቀጥተኛ ተጠቃሚ ከሆኑት ዓሳ አርቢዎችና አስጋሪዎች ፣በጀልባ ትራንስፖርት ከተሰማሩና እና የሆቴል እና ቱሪዝም ባለድርሻዎች ጋር በቅንጅት መስራት ከተቻለ የመከላከል ስራው ውጤታማ ይሆናል ብለዋል።

በተጨማሪ አረሙ አበባ ሳያወጣና ዘር ሳያፈራ ለይቶ በመንቀል አደጋውን በከፍተኛ መጠን መቀነስ እንደሚቻል ጥናቱን ዋቢ አድርገው ጠቅሰዋል።

አንዱ አበባ በአማካይ 4 ሺህ ዘር በማፍራት በፍጥነት ውሃ ውስጥ እራሱን በማባዛት በሃይቆች ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ያስከትላል ሲሉም ገልጸዋል።

የአረሙ ዘር ውሃ ውስጥ ከገባ ደግሞ የውሃ አካሉ ቢደርቅ እንኳን እስከ 30 ዓመት አፈር ውስጥ በመቀመጥ ውሃ ሲያገኝ እንደ አዲስ ያፈራል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ያለው የአየር ሁኔታ ለእምቦጭ አረም መራባት ተስማሚ ከመሆኑ ባሻገር የውሃ አካላት ብክለት ለአረሙ መስፋፋት አመቺ ሁኔታ መፍጠሩን አንስተዋል፡፡

በመሆኑም ወንዞችና የውሃ አካላትን ከብክለት መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አረሙን ኬሚካል በመጠቀም ማጥፋት የሚቻል ቢሆንም ኬሚካሉ ውድ በመሆኑ ሀይቆች ላይ ኬሚካል መጠቀም ከዋጋ አንጻር ከባድ መሆኑን ጠቁመዋል።

አረሙን የሚመገበውን ነፍሳት ከውጪ አገር በማምጣት ተራብቶ አረሙን እንዲበላው መልቀቅ ሌላው አማራጭ መሆኑንም አክለዋል።

ሆኖም ነፍሳቶቹ በሚፈለገው መጠን አረሙን ላይመገቡትና ከአረሙ ውጭ ሌሎች ዕጽዋትን ሊመገቡ ይችላሉ ብለዋል።

የእምቦጭ አረምን ለማጥፋት ካሉት ዘዴዎች አዋጩ መንገድ በእጅ በመንቀል አድርቆ ማቃጠል መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም