አሸባሪው ህወሃት በጎብዬ ከተማ ንጹሃንን በጅምላ ጨፍጭፏል፤ ነፍሰጡር እናቶችን ህክምና በመከልከል እንዲሞቱ አድርጓል

83

ታህሳስ 12/2014(ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት በጎብዬ ከተማ ንጹሃንን በጅምላ ከመጨፍጨፍ ጀምሮ ነፍሰጡር እናቶችን ህክምና በመከልከል እንዲሞቱ እስከማድረግ የደረሰ ግፍ ፈጽሟል፡፡

አሸባሪው ህወሓት በአማራና አፋር ክልሎች በወረራ በያዘባቸው አካባቢዎች ንጹሃንን በጅምላ ከመግደል በተጨማሪ ከፍተኛ የንብረት ዘረፋና ውድመት ፈፅሟል።

የሽብር ቡድኑ በሌሎች አካባቢዎች የፈጸመውን ግፍ በጎብዬ ከተማም ደግሞታል፡፡

የአሸባሪ ቡድኑ ወራሪ ኃይሎች በከተማዋ ንጹሃንን በጅምላ ጨፍጭፈዋል፤ ሴቶችን አስገድደው ደፍረዋል፤ ንብረት ዘርፈዋል፤ መውሰድ ያልቻሉትን ደግሞ አውድመዋል፡፡

በተጨማሪም ነፍሰጡር እናቶች ህክምና እንዳያገኙ በመከልከል እናቶችን ጨምሮ ጨቅላ ህጻናት እንዲሞቱ ማድረጋቸውንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ ነዋሪዎችን ህክምና በመከልከል በተለያዩ ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች እንዲሞቱ ማድረጋቸውንም እንዲሁ፡፡

አቶ ተስፋዬ ተሾመ የተባሉ የጤና ባለሙያ በህክምና አገልግሎት እጥረት ምክንያት በተለያዩ በሽታዎች ህይወታቸው ያጡ ሰዎች እንዳሉ ገልፀው የህክምና እርዳታ ለማድረግ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት እንግልት ይደርስባቸው እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡

ወጣት ሞላ ጎበዜ እና አቶ ሃይሉ መንገሻ በበኩላቸው አሸባሪ ቡድኑ በ6 ወር ቆይታው ብዙ በደል እንዳደረሰባቸው ጠቅሰው የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች ወደ ከተማዋ መግባት ዳግም እንደመወለድ መቁጠራቸው ይናገራሉ፡፡

የነዋሪዎችን ኪስ ከመፈተሽ ጀምሮ ከፍተኛ ዝርፊያ መፈጸማቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም ለችግር መዳረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

የአሸባሪ ቡድኑ አባላት ኪስ በመበርበር ብር ካገኙ ይወስዱ ስለነበረ በነፃነት መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው በጓዳ ውስጥ ተደብቀው ይኖሩ እንደነበረ አሁን ላይ ግን ደስታቸውን በመግለፅ ላይ መሆናቸውን ወይዘሮ ዜኒት እጅጉ ትገልፃለች፡፡

"በዘመቻ ለህብረብሔራዊ አንድነት" የተሰማራው ጥምር ኃይል ከተማዋን ከአሸባሪ ቡድኑ ነጻ በማውጣቱ  መደሰታቸውንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም