የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ለሁለት ተመራማሪዎች የመሪ ተመራማሪነት ማዕረግ ሰጠ

213
አዲስ አበባ  ግንቦት9/2010 የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በተቋምና በአገር ደረጃ  የምርምር ስርዓቱ ውስጥ ለረጂም ዓመታት በማገልገል  ጉልሕ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሁለት ተመራማሪዎች የሙሉ ተመራማሪነት ማዕረግ ሰጠ። እነዚህ ተመራማሪዎች ግንባር ቀደም በመሆን ልምዳቸውን ያካፈሉና የምርምር ስርዓቱን ቀጣይነት ባለው መልኩ ሲመሩና ሲያስቀጥሉ የቆዩ መሆናቸው ተረጋግጦ ነው ሙሉ የተመራማሪነት ማዕረግ የተሰጣቸው። በዚህም መሰረት በኢንስቲትዩቱ ዘንድሮ  ለሁለተኛ ጊዜ የሚሰጠውን በግብርና ምርምር ዘርፍ የመጨረሻ የእድገት ደረጃ ላይ የሚገኘውን የመሪ ተመራማሪነት ደረጃ መስፈርቶች  በብቃት ላሟሉት ዶክተር ጌታቸው አገኘሁ እና ዶክተር ቶሎሳ ደበሌ ለሁለተኛ ጊዜ የተዘጋጀውን የመሪ ተመራማሪነት  ማዕረግ ሰጥቷል። በምርምር ዘረፉ  በሰው ኃይል የካበተ ልምድ ያላቸውና ዛሬ ላይ አገሪቷ ለደረሰችበት የግብርና እድገት ውጤት እድሜያቸውን ሰጥተው ያልተቆጠበ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ የቆዩና እያደረጉ የሚገኙ ሁለቱ አንጋፋ ተመራማሪዎችን በመሪነት ማስቀመጡ ለተመራማሪዎች ክብርን የሚያጎናጽፍ ነው ብሏል ኢንስቲትዩቱ። የሁለቱ ተመራማሪዎች እውቅና መሰጠት ወደ ፊትም አገሪቷ በግብርናው ዘርፍ ልታሳካቸው ያስቀመጠቻቸውን ግቦች እውን ለማድረግ የማይተካ ሚና አለው ሲል ኢንስቲትዩቱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ  አስታውሷል። ተመራማሪዎቹ በምርምር ስርዓቱ ያካበቷቸውን ልምዶች፣ ለኅትመት ያበቋቸውን ጽሑፎች፣ ማሕበረሰቦችን በቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ በአቅም መገንባት ረገድ ያደረጓቸው ተግባራትና በምርምር ስርዓቱ ውስጥ፣ በምርምር ስራ አመራር የነበራቸው ድርሻም ከመስፈርት ውስጥ ገብቷል። መሪ ተመራማሪ ዶክተር ጌታቸው አገኘሁ ከ1991 ጀምሮ በተፈጥሮ ሀብት ምርምር፣ በአፈር ልማት የምርምር ዘርፍ፣ በተለይም በአፈር ለምነትና በአግሮኖሚ ምርምር ዘርፍ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር አውጥተዋል። በ2006 በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በ5ኛው አገር አቀፍ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን እውቅናና የሜዳሊያ ሽልማት ላይ በብቅል ገብስ ምርምር ዘርፍ የሜዳሊያ ተሸላሚ ነበሩ። ከግልና ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር ከ29 በላይ ጆርናል ጽሑፎችና 36 የተለያዩ ኅትመቶችን፣ በአጠቃላይ 65 ጽሑፎችን ለኅትመት በማብቃት ለግብርና ሳይንስ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ተመራማሪ ናቸው። ሁለተኛው መሪ ተመራማሪ  ዶክተር ቶለሳ ደበሌ  ደግሞ  ከ1982 ጀምሮ በአፈርና በውኃ ምርምር ፣ በአሲዳማ  አፈር ማሻሻያ  የምርምር ዘርፍ፣ የአፈር ማዳበሪያና አጠቃቀም፣ የኮምፖስትና የቨርሚ ኮምፖስት ቴክኖሎጂዎችን  ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር ሆነው በማውጣትና የተለያዩ የምርምር ፕሪጀክቶችን ነድፈው ሰርተዋል። በተጨማሪ  ዶክተር ቶለሳ  58 ያሕል ጽሑፎችን በማሳተም ለግብርና ሳይንስ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአገሪቷን የግብርና ዘርፍ በተለያዩ ችግር ፈቺ የግብርና ምርምር ቴክኖሎጂዎችና እውቀትን በማመንጨትና በማቅረብ ለአገራዊ ግብርና ምርትና ምርታማነት ማደግ እየሰራ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም