ኢትዮጵያዊያን እያደረጉት ያለው ድጋፍ “ጉዳት የደረሰበት ሕዝባችንን ለማቋቋም የሚያስችል ነው”

186

ባህር ዳር ታህሳስ 11/2014 “መላ ኢትዮጵያዊያን እያደረጉት ያለው ሁለንተናዊ ድጋፍ በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ጉዳት የደረሰበት ህዝባችንን ለማቋቋም የሚያስችል ነው” ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለጹ።

የኢፌዴሪ ፍትህ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ጠበቆችና የሕግ ባለሙያዎች ማህበር ጋር በመተባበር የ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር እና የአይነት ድጋፍ ለአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት አስረክበዋል።

ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት በክልሉ በወራራ በቆየባቸው አካባቢዎች ንጹሃንን በመግደል፣ ሀብት ንብረት በመዝረፍና በማውደም ጉዳት አድርሷል።

የሽብር ቡድኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ከቤት ንብረታቸው በማፈናቀልም የኢኮኖሚ፣ የሞራልና የስነ-ልቦና ጉዳት እንዲደርስባቸው ማድረጉንም ገልጸዋል።

“ ወራሪው ቡድን በህዝባችን ላይ ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ቢሆንም ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እያደረጉት ያለው ድጋፍ ተጎጂዎች የደረሰባቸውን የልብ ስብራት ለመጠገን የሚያስችል ነው ” ብለዋል።

“የፍትህ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎችና የጠበቆች ማህበር ዛሬ ያደረጋችሁት ድጋፍም ለወገናችሁ ያላችሁ አጋርነት ማረጋገጫ ነው” ሲሉም ዶክተር ይልቃል ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን እያደረጉት ያለው ትብብርና ድጋፍም ህዝባችን ከደረሰበት ሁለንተናዊ ጥቃት በፍጥነት በማገገምና በስነ ልቦና ተጽናንቶ ወደመደበኛ እንቅስቃሴው ፈጥኖ እንዲገባ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

የፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፍቃዱ ፀጋ በበኩላቸው “አሸባሪ ቡድኑ ያደረሰው መጠነ ሰፊ ጉዳትና ውድመት በአንድ ጊዜ አስተዋጽኦ ሊፈታ አይችልም” ብለዋል።

“በመሆኑም መንግሥት፣ መላ ኢትዮጵያዊያን እና ረጂ ድርጅቶች የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ሥራውን ለማሳካት በቀጣይ በጋራ ተረባርበን ልንሰራ ይገባል ሲሉ” ገልጸዋል።

በተጨማሪም በአሸባሪው ህወሓት የተወረሩ አካባቢዎችን ነፃ ለማውጣት በግንባር ጠላትን እየተፋለመ ላለው የወገን ጥምር ጦር ቀጣይነት ያለው ድጋፍ መስጠት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

ሚንስቴሩ ከሠራተኞቹ፣ ከኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች እና የጠበቆች ማህበር ጋር በመተባበር የ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የጥሬ ገንዘብና ተጨማሪ የደረቅ ምግብና አልባሳት ድጋፍ ለክልሉ ማስረከቡን ገልጸዋል።

በክልሉ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ነበሩበት አካባቢ በመመለስ ለማቋቋምና የፈረሱ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ከክልሉ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።