በመተከል ዞን ለውክልና ጦርነት የተሰለፉ ፀረ-ሰላም ሃይሎች ላይ የተጠናከረ እርምጃ ይወሰዳል

63

ታህሳስ 10/2014/ኢዜአ/ በመተከል ዞን ለውክልና ጦርነት የተሰለፉ ፀረ-ሰላም ሃይሎች ላይ የተጠናከረ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደሕንነት ጉዳዮች አማካሪ ገዱ አንዳርጋቸው ተናገሩ።

የአካባቢው ማህበረሰብም መንግስት በወንጀለኞች ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ በመደገፍ ተጠርጣሪዎችን  በማጋለጥና ተጠያቂ እንዲሆኑ በማድረግ ትብብራቸው እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ መተከል ዞን እየተስተዋለ ያለውን የጸጥታ ችግር ዘላቂ እልባት ማበጀት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ የአገር ሽማግሌዎችና የጎሳ መሪዎችን ያሳተፈ የሰላም ጉባኤ በግልገል በለስ ከተማ ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ ገዱ አንዳርጋቸው፤ በመተከል ዞን በየጊዜው በሚፈጠር የውክልና ጦርነት በርካታ ንጹሃን ለሞትና መፈናቀል መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር የሚሹ አካላት በሚያቀናብሩት ሴራ የአካባቢው ማህበረሰብ በፀረ ሰላም ሃይሎች በርካታ ችግሮች እየደረሱበት መሆኑንም አንስተዋል።

መንግስት ለችግሩ እልባት ለመስጠት የተለያዩ አማራጮችን ቢያቀርብም እስካሁንም በጥፋት መንገዳቸው የቀጠሉ ሃይሎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም መንግስት የዜጎችን ሰላም ለማስጠበቅ ለሚያደርገው ጥረት የሀገር ሽማግሌዎች፣ የጎሳ መሪዎች እና አጠቃላይ ማህበረሰቡ ከመንግስት ጎን በመቆም ጸረ ሰላም ሃይሎችን መታገል አለበት ብለዋል።

በመተከል ዞን ለውክልና ጦርነት የተሰለፉ ፀረ-ሰላም ሃይሎች ላይ መንግስት የተጠናከረ እርምጃ ይወስዳል ሲሉም አረጋግጠዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን፤ በዞኑ የውክልና ጦርነት አጀንዳ ያነገቡ አካላት በተላላኪዎቻቸው በኩል በህዝብ ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ መሆኑን ጠቅሰው በጥፋት ፈፃሚዎች ላይ የተጠናከረ እርምጃ እንወስዳለን ብለዋል።

የዞኑ የኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ሌተናል ጄነራል ሐሰን ኢብራሂም በበኩላቸው መንግስት በአካባቢው የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የመከላከያ ሠራዊትና የክልል ልዩ የጸጥታ ሃይል በዞኑ ማሰማራቱን ገልፀዋል።

በመሆኑም በዞኑ የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ሃይሎች እጃቸውን ለመንግስት እንዲሰጡ ጠይቀው፤ እጅ የማይሰጡ ካሉ ግን የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅተናል ብለዋል።

የጸጥታ ሃይሉ በወንጀለኞች ላይ ለሚወሰደው እርምጃ የአካባቢው ማህበረሰብ ተባባሪ እንዲሆንም ሌተናል ጄነራል ሐሰን ጠይቀዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በዞኑ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መንግስት የሚያደርገውን ጥረት በመደገፍ ጸረ ሰላም ሃይሎችን ለመዋጋት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም