ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ የማምረት አቅሟን ማሳደግና ዓለም ዓቀፍ የገበያ አማራጮቿን ማስፋት ይገባታል

81

ታህሳስ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጫናውን ለመመከት በአገር ውስጥ የማምረት አቅሟን ማሳደግና ዓለም ዓቀፍ የገበያ አማራጮቿን ማስፋት እንደሚገባት የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ገለጹ።

በኢትዮጵያ ጦርነት ከፍቶ ዘርፈ ብዙ ጥፋት እያደረሰ የሚገኘውን አሸባሪው ህወሃትን የሚደግፉ አንዳንድ ምእራባውያን አገራት በአገሪቱ ላይ ጫና በማድረግ ኢኮኖሚ ለማዳከም እየሰሩ እንደሚገኙ ይታወቃል።

በኢኮኖሚው ላይ የተፈጠረውን ጫና ለመቋቋም በተለይ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት ላይ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ኢዜአ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ጠቁመዋል።

ምርቶችን ከተለያዩ አገራት ለማስገባት የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለመቀነስ የውጭ ምርትን በአገር ውስጥ መተካት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የውጭ ምርትን በአገር ውስጥ የመተካት ጥረት አገሪቱ በምግብ ራሷን እንድትችል በማድረግ ረገድ ትልቅ ድርሻ እንዳለውም አብራርተዋል።

ኢትዮጵያውያን የአገር ወስጥ ምርቶችን የመጠቀም ባህላቸውን ማሳደግ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ደረጄ ደጀኔ አገሮች በኢኮኖሚ ማደግ የቻሉት የአገር ውስጥ የማምረት አቅምን በማሳደግ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ምርት ሲያድግ ከአገር ውስጥ ፍጆታ በላይ ለወጪ ንግድም እንደሚተርፍ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር ካሳ ተሻገር በበኩላቸው በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን ህብረተሰቡ እንዲጠቀማቸው ማድረግ ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።

ለአገር ውስጥ ምርት ያለው አመለካከት መሻሻልና መለወጥ እንዳለበትም ተናግረዋል።

ሌላው በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር አቶ መዚድ ናስር "ከውጭ የምናስገባቸውን ምርቶች አገር ውስጥ እንዲመረቱ ማበረታታት ያስፈልጋል” ብለዋል።

የግል ዘርፉ ተሳትፎ እንዲያደርግና የምርት አቅርቦት የሚሻሻልበትን የፖሊሲ አማራጭ መፈተሽ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ ልታቀርባቸው የምትችለው እና ያልተጠቀመችባቸው የግብርና እና ኢንዱስትሪ ውጤቶች አሏት።

በዚህም ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በማሳደግ በአውሮፓ፣ በእስያ እና በአፍሪካ አገራት ያሉ የገበያ አማራጮችን ማስፋት እንደሚገባም ነው የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎቹ ያስገነዘቡት።

የግብርና መር ኢኮኖሚውን ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚያስችሉ ስራዎችን በተጠናከረ ሁኔታ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።

የአገሪቱ ምርቶችና የፋብሪካ ውጤቶች የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆነው እንዲወጡ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።

መንግስት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ችግሮችን መፍታት ዓላማ ያደረገ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮጀክት ተግባራዊ እያደረገ እንደሆነ ይታወቃል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም