በተለያዩ ሀይቆች ላይ እየተስፋፋ የመጣውን የእምቦጭ አረም ለማጥፋት ህዝባዊ ንቅናቄ ያስፈልጋል

102

ታህሳስ 10/2014/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ የተለያዩ ሀይቆች ላይ እየተስፋፋ የመጣውን የእምቦጭ አረም ለማጥፋት ህዝባዊ ንቅናቄ አስፈላጊ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ ተናገሩ፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በዝዋይ ሀይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ማስወገድ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በባቱ ከተማ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነው።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ፤ በኢትዮጵያ የተለያዩ ሀይቆች ላይ እየተስፋፋ የመጣውን የእምቦጭ አረም ለማጥፋት ህዝባዊ ንቅናቄ ያስፈልጋል ብለዋል።

በዝዋይ ሀይቅ ላይ እየተስፋፋ የመጣውን የእምቦጭ አረም ለማጥፋት ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተደረገ ዘመቻ ከ9 ነጥብ 5 ሄክታር በላይ የሸፈነ አረም ማስወገድ ተችሏል፡፡

በባቱ ከተማ የሚገኙ 21 ድርጅቶች አረሙን ለማስወገድ ቦታ ተረክበው ወደ ስራ መግባታቸውን የተናገሩት ሚኒስትሩ በዚህ ዓመት 388 ሄክታር የሚሸፍን አካባቢን ከአረሙ ለማፅዳት ዕቅድ መያዙን ጠቁመው ለስኬቱ የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ከሚገኙ የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች መካከል የዝዋይ ሀይቅ አንዱ ሲሆን 31 ኪሎሜትር ርዝመት ሲኖረው ስፋቱ 20 ኪሎሜትር፣ ጥልቀቱ ደግሞ 9 ሜትር መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የዝዋይ ሐይቅ በዓሳ ምርቱ እንዲሁም በማራኪ የተፈጥሮ ሐብቶቹ ይታወቃል።

የእምቦጭ አረም የጣና እና ዝዋይ ሀይቅን ጨምሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ለተፈጥሮ ሃብት የህልውና አደጋ እየሆነ መጥቷል።

በመሆኑም የእምቦጭ አረምን ለማጥፋት የተደራጀና ቀጣይነት ያለው ህዝባዊ ንቅናቄ ያስፈልጋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም