ከዘንድሮ የመኸር ምርት ከ100 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል

87

ታህሳስ 10/2014/ኢዜአ/ ከዘንድሮ የመኸር ምርት ከ100 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በዘንድሮ የመኸር ወቅት 13 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ 375 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶም ወደ ስራ ተገብቷል።

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር መለስ መኮንን ለኢዜአ እንዳሉት የዘንድሮው የመኸር ሰብል አሰባሰብ በርካታ የህብረተሰብ ክፍል የተሳተፈበት መሆኑን ጠቅሰው ብክነትን ለመቀነስ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በምርት ዘመኑ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በርካታ የዝግጅት ስራዎች የተከናወኑ ቢሆንም አሸባሪው የህወሓት ቡድኑ በወረራ ይዟቸው በነበሩ የአማራና የአፋር ክልሎች ለመኸር እርሻ የተዘጋጀውን መሬትና ሰብል አውድሟል፣ ዘርፏል፣ አቃጥሏል።

የደረሰውን ውድመት ባካካሰ  መንገድ የምርት ስብሰባውን ለማካሄድ ከክልል ርዕሳና መስተዳድሮች ጋር በመነጋጋር  ስራው መጀመሩን አስታውሰዋል።

በዚህ የመኸር ወቅት ለመሰብሰብ ከታቀደው 375 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እስካሁን ከ35 በመቶ  በላይ የሚሆነው ምርት ተሰብስቧል ብለዋል።

በምርት አሰባሰብ ወቅት የሚያጋጥምን ብክነት ለመቀነስ በዘመናዊ የምርት አሰባሰብ ዘዴ የታገዘ ተግባር እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።

የዘማች ቤተሰቦችን ምርት ለመሰብሰብ የፌደራልና የክልል አመራሮችን ጨምሮ ተማሪዎችም በስፋት ተሳትፈዋል።

በአሸባሪው የህወሃት ቡድን የደረሰውን ውድመት ለማካካስ የውሃ አማራጭ ባለባቸው አካባቢዎች በመስኖ የታገዘ ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

የበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች እንዲከናወን በማድረግ ከ18 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ለማግኘት እየተሰራ ነው።

እስካሁን ከ154 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ዘር የተሸፈነ ሲሆን ይሀም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር የተሻለ አፈጻጸም ላይ እንዳለ ጠቁመዋል።

በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍም ከ310 ሺህ ሄክታር በላይ ምርት በዘር የተሸፈነ መሆኑን  ጠቁመዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድንና አንዳንድ ምዕራባውያን በአገሪቱ ላይ ያደረሱትን የኢኮኖሚ ጫና ለመመከት ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም