"ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ የጀግንነት ጥግ እያሳዩ ያሉ ሁሉ የላቀ ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል"

67

ታህሳስ 10/2014/ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ የጀግንነት ጥግ እያሳዩ ያሉ ሁሉ የላቀ ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

አሸባሪው ህወሓት በሴቶችና ህፃናት ላይ የፈፀመውን አስገድዶ መድፈር እና የጅምላ ግድያ የሚያወግዝ ሰልፍ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ የጀግንነት ጥግ እያሳዩ ያሉ ሁሉ የላቀ ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

በተለያዩ አውደ ውጊያዎች በቆራጥነት የተሰለፉ፤ በዓለም አደባባይ የ'በቃ" የተቃውሞ ንቅናቄን ያከናወኑ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ገድላቸውን ታሪክ የሚዘነጋው አይሆንም ብለዋል ከንቲባዋ።

ከንቲባዋ በመልእክታቸው "የእህቴ ጠባቂ ነኝ" በሚል መሪ ሃሳብ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርስን ጥቃት በጋራ ማስቆም አለብን ብለዋል።

በአማራና አፋር ክልሎች አሸባሪው ህወሃት ያደረሰው ኢ-ሰብአዊ ተግባርና ቁሳዊ ውድመት በተለይም በሴቶችና ህፃናት ላይ ያደረሰው አስነዋሪ ድርጊት ፈፅሞ ይቅር የማይባል ድርጊት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ማንኛውንም ያልተገባ የውጭ ጫና አትቀበልም ያሉት ከንቲባዋ በጊዜ ሂደት የዕውነትና የድል ብርሃኗ ደምቆ እንደሚታይ አንጠራጠርም ብለዋል።

በተሰማራንበት ግንባር ሁሉ በንቃት በመሳተፍ ለኢትዮጵያ ድል ስኬት ቀጣይነትና ሁለንተናዊ ብልፅግና መስራት አለብን ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው ፤ የሰው ዘር መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ የገዘፈና የጠለቀ የታሪክ ባለቤት በመሆኗ ኃያላን አገራት ሊከፋፍሏትና ታሪኳን ሊያደበዝዙት ተነስተዋል ብለዋል።

ለዚህም የእናት ጡት ነካሽ የሆኑ ባንዳዎች ኢትዮጵያን ወግተዋል፤ ጠባቂ ወታደሮችን በግፍ ጨፍጭፈው ክህደታቸውን በተግባር አሳይተዋል ነው ያሉት።

አሸባሪው ቡድን በተለይም በአማራና አፋር ክልሎች በወረራ በቆየበት ጊዜ በሴቶችና ህፃናት ላይ የፈፀመው ግፍ፣ ግድያና ዘረፋ የከፋ መሆኑን አንስተዋል።

የሽብር ቡድኑ አካል ጉዳተኞች ሳይቀሩ ለማመን የሚከብድ ግፍና ሰቆቃ የፈፀመባቸው ሲሆን፤ ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋማትንም አውድሟል።

ይህንን ከሃዲና ወንጀለኛ ቡድን በመዋጋት ሂደት መላው ኢትዮጵያዊያን ከዳር ዳር መነሳታቸውን ጠቅሰው፤  በአገር ህልውና ዘመቻው በተለይ ሴቶች የላቀ ሚናቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም በሁሉም የትግል ግንባሮች ለኢትዮጵያ ሕልውና ስንል የሚጠበቅብንን ሁሉ ለማድረግ መዘጋጀት አለብን ብለዋል ሚኒስትሯ።

ዓለምአቀፍ ተቋማትና ዓለምአቀፍ መገናኛ  ብዙኃን አሸባሪው ህወሓት በሴቶችና ህፃናት ላይ የፈፀመውን ወንጀል እንዲያጋልጡም ጠይቀዋል።

ከዚህ በተቃራኒ በህዝብ የተመረጠውን የኢትዮጵያ መንግስት እውቅና በመንፈግ የኢትዮጵያን ህልውና በመፈታተን ላይ ያሉ የውጭ ኃይሎችን በጥብቅ እናወግዛለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም