የኢትዮጵያ ሴቶች በአገር ህልውና ማስከበር ዘመቻው የላቀ ሚናቸውን እየተወጡ ነው

47

ታህሳስ10/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ሴቶች በአገር ህልውና ማስከበር ዘመቻው የላቀ ሚናቸውን እየተወጡ መሆኑን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ተናገሩ።

አሸባሪው ህወሓት በሴቶችና ህፃናት ላይ የፈፀመውን አስገድዶ መድፈር እና የጅምላ ግድያ የሚያወግዝ ሰልፍ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ እየተካሄደ ነው።

በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ የሴቶችና ህፃናት ጥቃት 'ይብቃ' ብላችህ ለተነሳችሁ ሁሉ ምስጋና ይገባችኋል ብለዋል።

የሰው ዘር መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ የገዘፈና የጠለቀ የታሪክ ባለቤት በመሆኗ ኃያላን አገራት ሊከፋፍሏትና ታሪኳን ሊያደበዝዙት ተነስተዋል ብለዋል።

ለዚህም የእናት ጡት ነካሽ የሆኑ ባንዳዎች ኢትዮጵያን ወግተዋል፣ ጠባቂ ወታደሮችን በግፍ ጨፍጭፈው ክህደታቸውን በተግባር አሳይተዋል ነው ያሉት።

አሸባሪው ቡድን በተለይም በአማራና አፋር ክልሎች በወረራ በቆየበት ጊዜ በሴቶችና ህፃናት ላይ የፈፀመው ግፍ፣ ግድያና ዘረፋ የከፋ መሆኑን አንስተዋል።

የሽብር ቡድኑ አካል ጉዳተኞች ሳይቀሩ ለማመን የሚከብድ ግፍና ሰቆቃ የፈፀመባቸው ሲሆን ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋማትንም አውድሟል።

ይህንን ከሃዲና ወንጀለኛ ቡድን በመዋጋት ሂደት መላ ኢትዮጵያዊያን ከዳር ዳር መነሳታቸውን ጠቅሰው  በአገር ህልውና ዘመቻው በተለይ ሴቶች የላቀ ሚናቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም በሁሉም የትግል ግንባሮች ለኢትዮጵያ ሕልውና ስንል የሚጠበቅብንን ሁሉ ለማድረግ መዘጋጀት አለብን ብለዋል ሚኒስትሯ።

አለም  አቀፍ ተቋማትና አለም አቀፍ መገናኛ  ብዙሃን አሸባሪው ህወሃት በሴቶችና ህፃናት ላይ የፈፀመውን ወንጀል እንዲያጋልጡም ጠይቀዋል።

ከዚህ በተቃራኒ በህዝብ የተመረጠውን የኢትዮጵያ መንግስት እውቅና በመንፈግ የኢትዮጵያን ህልውና በመፈታተን ላይ ያሉ የውጭ ሃይሎችን በጥብቅ እናወግዛለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም