'ዩኔስኮ' ቅርሶች ሲወድሙና እና ሲዘረፉ ዝምታን መምረጡ ከተቋቋመበት ዓላማ ሌላ አጀንዳ እንዳለው ያሳያል

85

ታህሳስ 10/2014/ኢዜአ/ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ቅርሶች ሲወድሙና እና ሲዘረፉ ዝምታን መምረጡ ከተቋቋመበት ዓላማ ሌላ አጀንዳ እንዳለው የሚያሳብቅ መሆኑን የታሪክና የሕግ መምህሩ ዶክተር አልማው ክፍሌ ተናገሩ።

አሸባሪው የህወሀት ቡድን ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች በርካቶችን ገድሏል አፈናቅሏል።

የሽብር ቡድኑ በህዝብና በመንግስት ንብረቶች ላይም የጥፋት እጆቹን አሳርፏል።

የእምነት ተቋማትን በማውደምና ቅዱሳት መጻህፍትን በማቃጠልም ሰይጣናዊ ስራውን በግልጽ አሳይቷል ።

ታሪካዊ ቦታዎችን ማፍረስ እና ቅርሶችን መዝረፍ ያልቻለውን ደግሞ ማውደም የተካነበትተግባሩ መሆኑም ተረጋግጧል።

ቅርስ የትም ይኑር የት የሰው ልጅ ሁሉ ሀብት ነው የሚሉት የታሪክና የሕግ መምህሩ ዶክተር አልማው አለም አቀፍ ተቋማት የአሸባሪ ቡድኑን አስነዋሪ ተግባራት እየተመለከቱ ዝምታን መምረጣቸው ተገቢ አለመሆኑን ይናገራሉ።  

በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በኢትዮጵያ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ዝምታን መምረጡ  ሚዛናዊነት የጎደለውና ከአንድ አለም አቀፍ ተቋም የማይጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ድርጅቱ ለምእራባውያን ጥቅም ብቻ የሚሰራ እና በትምህርት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሰበብ አገራት እንዲወረሩ የሚያደርግ ድርጅት ነው ብለዋል።

አሸባሪው ህወሀት የጥቂት ምእራባውያንን ፍላጎት ሲያስፈጽም እንደነበር ገልጸው ይህ ቡድን ሲመታ የእነሱም ህልም አብሮ መመታቱን ገልጸዋል።

አሁን ላይ በአሸባሪው ቡድን ቅርሶች ሲዘረፉና ሲወድሙ ዝምታን መምረጣቸው እኛ የምንፈልገውን ካልፈጸማችሁ ከሚል እሳቤ የመነጨ መሆኑን አስረድተዋል።

እነዚህ በምእራባውያን የሚዘወሩ ድርጅቶች ከቅርስ አልፈው አገር ለማፍረስ እየሰሩ ያሉ ድርጅቶች ናቸው ነው ያሉት።

ታላላቅ የሰው ልጆች ቅርስ የነበራት ኢራቅ ምእራባውያን ሰላም በማስከበር ሰበብ በመግባት ዝርፊያ እንደፈጸሙም ታሪክ እንደሚያሳይም ገልጸዋል።

ድርጅቱ ይህ ሁሉ ተግባር ሲፈጸም የማስቆም ሀላፊነት ነበረበት ያሉት ዶክተር አልማው ሆኖም በተቃራኒው የሽብር ቡድኑን እየደገፈ መሆኑን ገልጸዋል።

ቅርሶች የሰው ልጆች ሁሉ ሀብት እንደመሆናቸው ጥቃት ሲደርስባቸው ይህ ድርጅት ማስቆም እንዲሁም ተግባሩንም ማውገዝ እንደነበረበት ተናግረዋል።

ድርጅቱ ከዚህ ቀደም በቅርሶች ላይ ጉዳት አድርሰዋል ያላቸውን ቡድኖች የፈረጀ ሲሆን ለአብነትም ሂዝቦላን ቦኮሀራምን አልሸባብን አሸባሪ ማለቱን ገልጸዋል።

የአሸባሪው የህወሀት ቡድን ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን ለማጥፋት የተነሳ ድርጅት በመሆኑ ቅርሶችን ማጥፋቱ የማፍረስ አላማው አንዱ ተግባር መሆኑንም ነው የገለፁት።

ድርጅቱ ቅርሶችን እጠብቃለሁና አድሳለሁ ቢልም በኢትዮጵያ ቅርሶች ሲጎዱ ግን ዝምታን መርጧል ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን በመተባበር ከመንግስት ጋር በመሆን ይህ የሽብር ቡድን በቅርሶች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ርብርብ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚህ ሳምንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በተባበሩት መንግስታት ስር የሚገኙ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ስለደረሰው ጉዳት ዝምታን መምረጣቸው እንዳሳዘነው መግለጹ ይታወሳል።

የተ.መ.ድ የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ)ም ታሪካዊ ቅርሶችን ደኅንነትን በተመለከተ ምንም አለማለቱ እንዳስገረመውም ነበር የገለጸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም