የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመከላከል በሀገሪቱ ሰላምን ለማጎልበት ምሁራን ሚናቸውን እንዲያሳድጉ ተጠየቀ

140

ጂግጂጋ ፤ታህሳስ 9 ቀን 2014(ኢዜአ) አሜሪካን ጨምሮ የአንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነትን በመከላከል ሰላምን ለማጎልበት ምሁራን ሚናቸውን እንዲያሳድጉ ተጠየቀ።

የሰላም ሚኒስቴር ከጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ''የኢትዮጵያ የሰላም  ፖሊሲና ለሀገራዊ መግባባት መጎልበት የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ሚና" በሚል ርዕስ ያዘጋጀው የምክክር መድረክ  በሱማሌ ክልል ዋና ከተማ  ጅግጅጋ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሄራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ እንደተናገሩት ፤ ምሁራን በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ብሔራዊ መግባባት እንዲጎለብት ሚናቸውን ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል።

ለዚህም አዳዲስ ሃሳቦችን የማመንጨት፣የመተንተን፣የማሰራጨትና ማህበረሰቡን በማንቃት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ የምዕራባዊያን ሀገራት ኢትዮጵያን ለማንበርከክ በወንድማማች ህዝቦች መካከል ግጭት ፈጥረው ሃብት ለመዝረፍና ከተመጽዋች እንዳትወጣ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በማጋለጥም የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ከሉዓላዊነት፣ሀገራዊና ቀጠናዊ ትስስርና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ጣልቃ ገብነትን ለመመከት ሚናቸውን እንዲያጎለብቱም ሚኒስትር ዴኤታው አመልክተዋል።

ሚኒስቴሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በሀገሪቱ ሰላምና አንድነት ለማስፈን በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

''ኢትዮጵያ በውስጥም ሆነ በውጭ ጠላቶች የማትንበረከክና ችግሯን በራሷ መፍታት የምትችል ታላቅ ሀገር ናት'' ያሉት የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር በሽር አብዱላሂ ናቸው።

ዩኒቨርሲቲው አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት  ከኢትዮጵያ ይሁንታ ውጭ ጫና ለመፍጠር የሚያደርጉትን ሴራ ለማክሸፍ በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ምሁራን አሸባሪው ህወሃት  በከፈተው ጦርነት የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋምና ያወደማቸውን የመሰረተ ልማት ተቋማት መልሶ በማደራጀት ሚና መጫወት ይገባናል በማለትም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የሰላም ሚኒስቴር አመራሮች፣ የምስራቅ ኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተወካዮች፣የሱማሌ ክልል እና የአጎራባች የፀጥታ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በምክክር መድረኩ እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም