ሴቶች ኢትዮጵያን ለማዳከም ብሎም ለማፍረስ የተነሳውን ጣላት እንደቀደምት እንስት አርበኞች በጀግንነት ሊፋለሙት ይገባል

69

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ሴቶች ኢትዮጵያን ለማዳከም ብሎም ለማፍረስ የተነሳውን የጣላት ኃይል እንደቀደምት እንስት አርበኞች በጀግንነት ሊፋለሙት ይገባል" ሲሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ ገለፁ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ30ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ የሚከበረው የፀረ-ፆታዊ ጥቃት ቀን የማጠቃለያ መርሃ-ግብርን በአገር አቀፍ ደረጃ በውይይት መድረክ ተከብሯል።

በውይይቱ የሃይማኖት አባቶች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ከተለያዩ አገሪቱ ክፍሎች የመጡ ሴቶችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

ምክትል አፈ-ጉባኤዋ በዚህን ወቅት ኢትዮጵያ በአንድ በኩል ከድህነት ተላቃ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለመሆን እየተጋች፤ በሌላ በኩል ደግሞ በህልውናዋ የመጡ ጠላቶቿን እየተፋለመች ትገኛለች ነው ያሉት፡፡

አሸባሪው በአፋርና አማራ ክልሎች በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በሴቶች፣ ህጻናትና አረጋዊያን ላይ "ልብን የሚያደማ ግፍ" ፈጽሟል ብለዋል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ ይህን ግፍ የፈጸመው የኢትዮጵያን ህልውና ከማይፈልጉ የውጭ ጠላቶች ጋር በመቀናጀት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ካለው ፍላጎት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ሴቶች የኢትዮጵያን ጠላቶች በመመከት ረገድ የሚጠበቅባቸውን ሚና ሲወጡ መቆየታቸውን ገልጸው፤ አሁንም እንደ ቀደምት እንስት አርበኞች የኢትዮጵያን ጠላቶች በጀግንነት ሊፋለሙ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው አሸባሪ ቡድኑ በሴቶችና ህፃናት ላይ ያደረሰውን ኢ-ሰብዓዊና አረመኔያዊ ድርጊት በማስረጃ ሰንዶ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ማሳወቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አካባቢን በመጠበቅ፣ ወደግንባር በመዝመትና መከላከያ ሰራዊቱን በመደገፍ አሸባሪውን ቡድን ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት መደገፍ እንደሚገባም አስረድተዋል።

ለፆታዊ ጥቃትና ለችግር የተጋለጡ ሴቶችና ህፃናትን በመታደግ የተከፈተውን የውጭና የውስጥ ወረራ ለማስቆም አስተዋፅኦ ማበርከት አለብን ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም