በውጭ አገራት የሚኖሩ ኤርትራዊያንን ጨምሮ የሌሎች አገራት ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ፍላጎት አሳይተዋል

74

ታህሳስ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) በውጭ አገራት የሚኖሩ ኤርትራዊያንን ጨምሮ የሌሎች አገራት ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ፍላጎት ማሳየታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው በእንግሊዝና በአሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በመላው ዓለም ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራዎች ወደ አገር ቤት እንዲመጡ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት የዳያስፖራው ማህበረሰብ አባላት ሌሎች የውጭ አገር ዜጋ ጓደኞቻቸውንና ወዳጆቻውን ወደ ኢትዮጵያ እንዲሄዱ ቅስቀሳ እየተደረገ መሆኑን በማንችስተር ከተማ የሚኖረው ጋዜጠኛ አበበ ቶላ (አቤ ቶክቻው) ለኢዜአ ገልጿል።

ለኢትዮጵያ ወዳጆች "ባክ ቱ ዘ ኦሪጅን" ወይም "ወደ ቀደምት የሰው ዘር መገኛ ይምጡ" በሚል እሳቤ ወደ  ምድረ ቀደምት አገር ኢትዮጵያ እንዲመጡ ጥሪ እየተደረገ መሆኑንም አመልክቷል።

እየተደረጉ ባሉ ቅስቀሳዎች በርካታ የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ፍላጎት ማሳየታቸውንና ይሄም ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግሯል።

በተጨማሪ በእንግሊዝ ለሚገኙ የኢትዮጵያ ወዳጆች በኢትዮጵያ ያለውን እውነታ የማስረዳት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ነው ጋዜጠኛ አበበ የገለጸው።

በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ የሚኖሩት አቶ ደሳለኝ አበራ በበኩላቸው ከኢትዮጵያውያንና ከትውልደ ኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ኤርትራውያን እና ሌሎች የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ቤት እንደሚመጡ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ወዳጅ አገር ኤርትራ ዜጎች በቀረበው ጥሪ አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ያላቸው ፍላጎት አስደሳች መሆኑንም ገልጸዋል።

በአሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ የማሳወቁ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰው፤ በዚህም በርካቶች ጥሪውን ተቀብለው ወደ አገር ቤት ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ዳያስፖራዎች ቢያንስ አንድ የውጭ አገር  ዜጋ ወደ ኢትዮጵያ ይዘው እንዲመጡ ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም