በአማራ ክልል ከ88 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለምቷል

91

ባህር ዳር፣ ታህሳስ 9/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሓት የጠፋውን የመኸር ምርት ለማካካስ በተካሄደ የመስኖ ልማት ንቅናቄ እስካሁን ከ88 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የመስኖ ልማት ባለሙያ አቶ ተሻለ አይናለም እንደገለጹት በጦርነቱ ምክንያት ሊቀንስ የሚችለውን ምርት ሰላም በሆኑ አካባቢዎች የመስኖ ልማት ሥራው ቀድሞ እንዲጀመር ተደርጓል።

በክልሉ በዘንድሮው የበጋ ወቅት ወደ 240 ሺህ የሚጠጋ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዶ እስካሁን ባለው እንቅስቃሴ 88 ሺህ 482 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል።

የደረሱ ሰብሎችን በማንሳት በመስኖ ልማቱ ፈጥነው የሚደርሱ አዝርዕት፣ አትክልት፣ ስራስር፣ ቅመማቅመም በመሳሰሉት ማልማት እንደተቻለ ተናግረዋል።

ባለሙያው እንዳሉት ዘንድሮ በመስኖ ለማልማት በእቅድ የተያዘው መሬት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ9 ሺህ ሄክታር መሬት ብልጫ አለው።

የመስኖ ልማቱን ምርታማነት ለማሳደግ እስካሁን ድረስ ከ94 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያና 39 ሺህ 426 ኩንታል ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ መዋሉንም ገልጸዋል።

በመስኖ ልማቱ ከ1 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች ይሳተፋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን እስካሁንም 381 ሺህ ያህል አርሶ አደሮች ወደ ሥራ ገብተዋል።

በመስኖ ልማቱ የተሳተፉ አርሶ አደሮች ልማቱን እያካሄዱ ያሉት  ዘመናዊ ግድቦችን፣ በአቅራቢያቸው የሚገኙ ወንዞችን፣ ኩሬዎችንና ምንጮችን ተጠቅመው መሆኑን ጠቁመዋል።

እንዲሁም በመስኖ ልማቱ የተሳተፉ አርሶ አደሮች ውጤታማ እንዲሆኑ 46 ሺህ 300 ያህል የውሃ መሳቢያ ሞተሮችም ጥቅም ላይ መዋላቸውን ተናግረዋል።

የመስኖ ልማቱ እየተካሄደ ያለው በምዕራብ አማራ ዞኖች ውስጥ መሆኑን የተናገሩት ባለሙያው፣ በቀጣይም ከወራሪው ኃይል ነፃ በወጡ አካባቢዎችም እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

በክልሉ በዘንድሮው የበጋ ወቅት በመስኖ ከሚለማው መሬት 52 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ባለሙያው አስታውቀዋል።

በባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ የይጎማ ሁለቱ ቀበሌ አርሶ አደሮች መካከል አቶ አደባባይ ሰማ በሰጡት አስተያየት ከሁለት ሄክታር በላይ ማሳ በጤፍ፣ በሽንኩርትና ቃሪያ በመስኖ ማልማታቸውን ገልጸዋል።

ከዚሁ የእርሻ ማሳ 200 ኩንታል ሽንኩርትና ቃሪያ እንዲሁም ስድስት ኩንታል የጤፍ ምርት እንደሚጠብቁም ተናግረዋል።

ሌላው የእዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ተወልኝ ደሌ ሁለት ሄክታር መሬት በቀይ ሽንኩርትና ጤፍ በመስኖ እያለሙ መሆናቸውን  ተናግረዋል።

አቶ ተወልኝ  አክለውም "ባለፉት ዓመታት ከመስኖ ልማቱ ያገኘሁት ተጨማሪ ገቢ ልጆቼን የተሻለ ትምህርት ቤት በማስተማር ጥሩ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ አግዞኛል" ብለዋል።

በክልሉ አምና በመስኖ ከለማው መሬት ከ37 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም