የዞኑ ሴቶች ለመከላከያ ሰራዊት ከ7 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

159

አዳማ ፣ ታህሳስ 08/2014(ኢዜአ) የምስራቅ ሸዋ ዞን ሴቶች አደረጃጀት ለመከላከያ ሰራዊት በጥሬ ገንዘብና በአይነት ከ7 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ።

የዞኑ ሴቶች ፌዴሬሽን ሃላፊ ወይዘሮ ፎዚያ ረሽድ “የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከአባቶቻችን የተረከብናትን ሀገር ሉዓላዊነትና ዳርድንበር እንዲከበር ውድ ህይወቱን እየገበረ ይገኛል” ብለዋል።

ፌዴሬሽኑና የሴቶች ማህበር በዞኑ በሚገኙ 10 ወረዳዎችና ሁለት የከተማ መስተዳድሮች ያሉትን አደረጃጀቶቹን በማስተባበር ለሶስተኛ  ጊዜ 5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የሚገመት የአይነት ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

ከአይነት ድጋፉ ውስጥ 391 ኩንታል ደረቅ ስንቅ እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል።

በተጓዳኝም በጥሬ ገንዘብ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ተሰብስቦ ድጋፍ ማድረጉን አመልክተዋል።

“የሀገራችን ሉዓላዊነት ሲደፈር ቁጭ ብለን የምናይበት ሞራል የለንም፤ ሁላችንም አደረጃጀቶቻችንን በማስተባበር ስንቅ በማዘጋጀት ለመከላከያ እያቀበልን ደጀንነታችን እያረጋገጥን ነው” ብለዋል።

“ለመከላከያ ድጋፍ ከማድረግ በተጓዳኝ በየደረጃው ያለውን አደረጃጀቶቻችን በማስተባበርና ህዝብን በማሳተፍ ከ11ሺህ 428 ሄክታር መሬት ላይ የደረሰ የዘማች ቤተሰብ ሰብል ሰብስበናል ” ያሉት ደግሞ የዞኑ ሴቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ወይዘሮ አያንቱ ተስፋዬ ናቸው።

ከዞን ጀምሮ እስከ ቀበሌ ያሉ የሴቶች ማህበራት አባላት የዘማች ቤተሰብ አባላትን በቁሳቁስ፣ በገንዘብና በአልባሳት ለመደገፍ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በባለቤትነት እንዲመሩት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል ።