የፌደራል ፖሊስ በወንጀል ምርመራ ወቅት በዜጎች ሰብአዊ መብት ላይ ጥሰት እንዳይፈጸም የሚያግዝ ቴክኖሊጂ ዘረጋ

187

ታህሳስ 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ የዜጎችን ሰብአዊ መብት አያያዝና አጠባበቅ መሰረት አድርጎ እንዲከናወን የሚያስችል ዘመናዊ አሰራር መዘርጋቱን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ የ10 አመት እቅዱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ አቅርቧል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የተቋሙን የአስር አመት እስትራቴጂክ እቅድ የትኩረት አቅጣጫዎች አመላክተዋል።

መረጃና ማስረጃ መር የላቀ የወንጀል ምርመራ አቅምን ማሳደግ የስትራቴጂክ እቅዱ አንዱ የትኩረት መሰክ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚሀም የታክቲክ የወንጀል ምርመራ ስራን እውቀትና ክህሎት ባላቸው ባለሙያዎች ማደራጀትና በቴክኖሎጂ መደገፍ በአስር አመቱ ትኩረት ከተሰጣቸው ተግባራት መካከል መሆኑን ተናግረዋል።

የምርመራ ተግባራት የዜጎችን ሰብአዊ መብት አያያዝና አጠባበቅ መሰረት አድርገው እንዲከናወኑ እያንዳንዱን የምርመራ ሂደት በቀጥታ መከታተል የሚያስችል ቴክኖሎጂ መዘርጋቱን አስረድተዋል።

አሰራሩ መርማሪ ፖሊስ ከተጠርጣሪ ቃል ሲቀበልና ቃለመጠየቅ ሲያደርግ ምስልና ድምጹን በቀጥታ መከታተል የሚያስችል ነው ብለዋል።

መርማሪ ፖሊስ የተጠርጣሪውን ቃል በሚቀበልበትና በሚመረምርበት ወቅት የምርመራ ቢሮ ሃላፊው ቢሮ ሆኖ በቀጥታ መከታተል የሚያስችል ነው።

ሃላፊው ባይኖር እንኳን ቴክኖሎጂው እያንዳንዱን የመረጃ ልውውጥ ስለሚቀዳ  የተቀዳውን በማየት ምርመራው የተካሄደበትን መንገድ መከታተል ያስችላል።

በቴክኖሎጂው ክትትል በማድረግ  ከተጠርጣሪዎች ጥቅም ፈልገው ያልተገባ ስራ ሲሰሩ የተደረሰባቸው አንዳንድ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቅሰዋል።

አሰራሩ የሰለጠኑ አገሮች ለወንጀል ምርመራ የዘረጉትና የሚጠቀሙበት አሰራር መሆኑን ኮሚሽነር ጀነራሉ ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ የዘረጋውን አሰራር “የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና ሌሎች የአገር ውስጥና የውጭ ተቋማት ተመልክተው ምስክርነት መስጠታቸውንም ጠቁመዋል።

አሰራሩ ፌደራል ፖሊስ ማንኛውንም ተጠርጣሪ ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ መብቱን አክብሮ በህጉ መሰረት የሚጠየቅበትን ስርአት ለመፍጠር አግዞታል ብለዋል።

በቀጣይም እንዲህ አይነቱ አሰራር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰው ቋሚ ኮሚቴው ክትትል እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በቀጣይ አስር አመታት የሽብር ጥቃቶችን በመከላከል፣ በወንጀል ምርመራ፣ በሰው ሃይል ልማት፣ በግዙፍ ፕሮጀክቶች ጥበቃና በሌሎች የአገርና ህዝብን ደህንነት ለማስጠበቅ በያዛቸው እቅዶች ላይ ገለጻ ተደርጓል።

የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ እጸገነት መንግስቱ ፌደራል ፖሊስ እቅዱን ማሳካት እንዲችል ቋሚ ኮሚቴው ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርግባቸውን ስልቶች መንደፉን  ተናግረዋል።

ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በቀጣይ አስር አመታት በአፍሪከ ከሚገኙ ምርጥ 5 የፖሊስ ተቋማት የመሆንና ሙያዊ ብቃትን ያረጋገጠ፣ አካታችና በህዝብ ታማኝ የሆነ ዘመናዊ የፖሊስ አገልግሎት ተፈጥሮ የማየት ራርዕይ አስቀምጦ እየሰራ ይገኛል።