ፓርቲው በመዲናዋ ለሚገኙ የዘማች ቤተሰቦች የአይነት ድጋፍ አደረገ

64

ታህሳስ 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) የብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት በመዲናዋ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች ለሚገኙ 220 ለሚሆኑ የዘማች ቤተሰብ አባላት የአይነት ድጋፍ አድርጓል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት አመራሮችና ሠራተኞች በአሸባሪው ህወሓት የተቃጣውን ሀገር የማፍረስ ሴራ ለመመከት በግንባር ለተሰለፉ የዘማች ቤተሰቦች አጋርነታቸውን ለማሳየት ድጋፍ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ካሊድ አልዋን የኢትዮጵያን ህልውና ለማረጋገጥ ዜጎች በተለያዩ ግንባሮች በመሰለፍ የበኩላቸውን ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

እየተካሄደ ባለው የህልውና ዘመቻ በግንባር ተሰልፈው ለህብረብሄራዊ አንድነት ዋጋ እየከፈሉ ያሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ የእነዚህን ዘማች ቤተሰቦች መደገፍ የዜግነት ግዴታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም የጽህፈት ቤቱ አመራሮችና ሠራተኞች በመዲናዋ ለሚገኙ የዘማች ቤተሰብ አባላት የአይነት ድጋፍ ማድረጋቸውን በመግለጽ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድወሰን ፍላቴ በበኩላቸው፤ በአዲስ አበባ ከሚገኙ 11 ክፍለ ከተሞች ለ220 የዘማች ቤተሰብ አባላት ድጋፍ መደረጉን ነው የገለጹት፡፡

ጀግኖቻችን በግንባር ተሰልፈው የሚያሳዩትን አርበኝነት እዚህ ያለን የህብረተሰብ ክፍሎች አካባቢያችንን ከጸረ ሰላም ሀይሎች መጠበቅና ፀጉረ-ልውጦች ሲያጋጥሙን ለፖሊስ በመጠቆም ለአካባቢያችን ዘብ ልንቆም ይገባል ብለዋል፡፡

ድጋፍ ከተደረገላቸው የዘማች ቤተሰቦች መካከል ወይዘሮ የውብዳር ከበደ ልጃቸው ለሀገሩ ሲል እየከፈለ የሚገኘውን ተጋድሎ በማስታወስ፤ ለመሰረታዊ ፍጆታ የሚሆን የአይነት ድጋፍ ስለተደረገላቸው አመስግነዋል፡፡ልጃቸውም "በአሸባሪዎች ሀገር አትፈርስም!" በማለት ለሀገሩ የበኩሉን አሻራ ለማሳረፍ ወስኖ በመዝመቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

ወይዘሮ ብዙዬ ካሳሁን በበኩላቸው ባለቤታቸው ሀገር እንዳትደፈርስ መዝመቱን ገልጸው፤ ጽህፈት ቤቱ ይህን አስታውሶ እንደዚህ አይነት እገዛ በማድረጉ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

ዘማቾች የኢትዮጵያን ህልውና ለማስከበር ዋጋ ሲከፍሉ እኛም የመዲናዋ ነዋሪዎች አንዳንድ ሰርጎ ገቦች በመካከላችን በመግባት የከተማዋን ፀጥታ እንዳያውኩ የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም