ሚኒስቴሩ አረጋዊያንን ለመደገፍ የጀመረውን የመኖሪያ ቤት ግንባታ እንደሚያጠናክር አስታወቀ

88

ጋምቤላ፤ ታህሳስ 8/2014(ኢዜአ) በጋምቤላ ከተማ ለአረጋዊያን መኖሪያ ቤት በመስራት የጀመረውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ አስታወቁ።

ሚኒስቴሩ ባለፈው ክረምት በጋምቤላ ከተማ ለአረጋዊያን የገነባቸውን መኖሪያ ቤቶችን  አስረክቧል።

በርክክቡ ሥነ-ሥርዓት ወቅት ሚኒስትሯ እንዳሉት፤ መስሪያ ቤታቸው ከግል ባለሃብቶችና ከክልሉ መንግስት ጋር በመቀናጀት የጀመረውን አረጋዊያንን የመደገፍ ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል።

ባለፈው ክረምት በጋምቤላ ከተማ የተጀመረው ለአረጋዊያን ቤቶችን የመገንባት ሥራ በቀጣይም አስፋፍተው ለማስቀጠል  ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል።

ተቋሙ ቤት ከገነባላቸው አረጋዊያን ጎን በመሆን ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ  ነው ሚኒስትሯ  ያረጋገጡት።

የጋምቤላ ክልል  ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ፤ ሚኒስቴሩ ለአረጋውያን ላደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ እንዲህ ያለው በጎ ተግባር በሌሎች አካላትም መለመድ እንዳለበት አመልክተዋል።

ቤት ከተገነባላቸው አረጋዊያን መካከል ወይዘሮ ሎሚ ጀርጀራ በሰጡት አስተያየት፤ ቤታቸው በመፍረሱ ምክንያት በተለይ በዝናብ ወቅት ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁን ቤታቸው በተሻለ ሁኔታ በመገንባቱ ችግራቸው መቃለሉንና  በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ ድጋፉን ላደረጉላቸውም  ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም