በአዲስ አበባ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ ታሪፍ ላይ ማሻሻያ ተደረገ

139

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 08/2014(ኢዜአ) አዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገው የትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ ታሪፍ ማሻሻያ አደረገ።

የተደረገው የታሪፍ ማሻሻያ ለሚኒ ባሶች እና ሚዲ ባሶች (ሃይገርና ቅጥቅጥ ባሶች) ብቻ እንጂ የብዙኃን ትራንስፖርት /ሸገር፣ አንበሳ ባስ/ የመሰሉ የትራንስፖርት አገልግሎቶችን እንደማይመለከት ተመላክቷል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ይርጋለም ብርሃኔ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ቢሮው የታሪፍ ማሻሻያው ዓለም አቀፉን የነዳጅ ዋጋንና የኅብረተሰቡን የመክፈል አቅም ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።

ማሻሻያው ከተማዋ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ጤናማ ለማድረግና የግሉ ዘርፍ በነዳጅ ዋጋ ማሻሻያው ምክንያት የኢኮኖሚ ኪሳራ እንዳይደርስበት ታስቦ የተደረገ መሆኑን ነው የገለጹት።

በዚህም መሰረት ጭማሪው በሚዲባስ (ሃይገርና ቅጥቅጥ) በኪሎ ሜትር በፊት ከነበረው 40 ሳንቲም ወደ 45 ሳንቲም ያደገ ሲሆን በሚኒባስ ታክሲ ላይ ከ90 ሳንቲም ወደ 1 ብር ከፍ ማለቱን ጠቁመዋል።

በሚዲ ባስ ዝቅተኛው የታሪፍ መጠን ጭማሪ 1 ብር ከፍተኛው 2 ብር መሆኑን ገልጸው በሚኒ ባስ ታክሲ ደግሞ ዝቅተኛው ጭማሪ 50 ሳንቲም ከፍተኛው ደግሞ 3 ብር ከ50 ሳንቲም መሆኑንም ተናግረዋል።

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኅብረተሰብ ክፍሎች የብዙኃን ትራንስፖርት ተጠቃሚ መሆኑን ጠቅሰው የታሪፍ ማሻሻያው እነዚህን የብዙኃን ትራንስፖርትን እንደማይመለከት ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ከታሪፍ በላይ ማስከፈልና መስመር ማቆራረጥ የመሰሉ ሕገ-ወጥ ተግባራትን የሚቆጣጠሩ 350 በላይ የሚሆኑ የሥምሪትና የቁጥጥር ሠራተኞች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

የትራፊክ ቁጥጥር ሠራተኞችና ትራፊክ ፖሊሶችም በዚህ ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ ተናግረዋል።

እነዚህ አካላት ተቀናጅተው እንዲሰሩ አቅጣጫ እንደተሰጣቸው ጠቁመው፤ ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ አካላት ለመከላከል መደበኛና ድንገተኛ ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል።

ኅብረተሰቡም መሰል ችግር ሲያጋጥመው ለሚመለከተው አካል ጥቆማ ማቅረብ እንደሚችልም ተናግረዋል።  

በከተማዋ ከ8 ሺህ በላይ ሚኒና ሚዲባሶች እንዲሁም ከ 1 ሺህ በላይ የብዙኃን ትራንስፖርት ሰጪ ተሽከርካሪዎች ይገኛሉ።

የብዙሃን ትራንስፖርት ሰጪዎች በቀን 1 ሚሊዮን ኅብረተሰብ የሚያጓጉዙ ሲሆን የሚኒና ሚዲ ባሶች ደግሞ እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎችን በቀን ያጓጉዛሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም