የአገር ውስጥ የመድኃኒት ምርትና አቅርቦትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው

59

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8/2014/ኢዜአ/ የአገር ውስጥ የመድኃኒት ምርትና አቅርቦት በማሳደግ አገሪቷ ለመድኃኒት ግዥ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ከኢትዮጵያ የመድኃኒትና ሕክምና መገልገያ አምራቾች ማኅበር ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን ሰነድ ዛሬ ተፈራርሟል።

ሰነዱን የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አብዱልቃድር ገልገሎና የኢትዮጵያ የመድሃኒትና ሕክምና መገልገያ አምራቾች ማኅበር ፕሬዘዳንት አቶ ዳንኤል ዋቅቶሌ ፈርመውታል።

በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደገለጹት፤ በአገሪቱ  ያለውን የመድሃኒት አቅርቦት ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡  

በተጨማሪ አገሪቱ ለመድኃኒት ግዥ የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለመቀነስ የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ ስምምነቱ የአገር ውስጥ የመድኃኒት ምርትና አቅርቦትን እንደሚያሰፋና ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ነው ያነሱት።    

ከዚህ በተጓዳኝ የአገር ውስጥ መድሃኒት አምራቾች በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ መንግሥት የተለያዩ ድጋፎች እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር አብዱል ቃድር ገልገሎ በበኩላቸው ከሚያቀርቧቸው መድኃኒቶች መካከል 20 በመቶው ብቻ ከአገር ውስጥ አምራቾች እንደሚያገኙ ጠቁመዋል።

ቀሪው 80 በመቶ የሚሆነው ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንደሚገባ ገልጸው፤ ስምምነቱ አምራቾች ምርቶቻቸውን በብዛትና በጥራት እንዲያቀርቡ ያስችላል ብለዋል።

ይህም በዘርፉ ከፍተኛ ለውጥ እንዲመጣ ያስችላል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ የመድሃኒትና የሕክምና መገልገያ አምራቾች ማኅበር ፕሬዘዳንት አቶ ዳንኤል ዋቅቶሌ በበኩላቸው በአገር ውስጥ የሚመረቱት መድኃኒቶች መጠን አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በመንግስት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ይበልጥ ሲጠናከሩ ወደ 40 በመቶ የመድኃኒት አቅርቦት በአገር ውስጥ ለመሸፈን የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም