በሰሜን እዝ ላይ የተፈፀመውን አሰቃቂ ድርጊት በዝምታ ያለፉ የምእራቡ ዓለም ሚዲያዎች አሁንም በሀሰት ዘገባ ላይ ተጠምደዋል

63

ታህሳስ 8/2014/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ የተፈፀመውን አሰቃቂ ድርጊት በዝምታ ያለፉ የምእራቡ ዓለም ሚዲያዎች አሁንም በኢትዮጵያ ጉዳይ ተከታታይ የሃሰት ዘገባ እያቀረቡ መሆኑን አሜሪካዊቷ ጋዜጠኛ አና ጋሪሰን ተናገረች።

ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ ያደረገችው ጋዜጠኛ አና ጋሪሰን ምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን በተለይ ደግሞ ሲኤንኤን አሸባሪውን ህወሃት በግልጽ ደግፎ መቆሙን ትናገራለች።

በጥቅምት 24 ቀን 2013 በኢትዮጵያ መከላከያ ሃይል የሰሜን ዕዝ ላይ አሸባሪው ህወሃት የፈፀመውን አሰቃቂ ጥቃት ችላ በማለት በተቃራኒው መንግስትን የሚወቅሱ ዘገባዎች ላይ ያተኮሩ የምእራቡ ዓለም ሚዲያዎች እንደነበሩ ታስታውሳለች።

በተለይም የሲኤን ኤን ዘገባ በሰራዊቱ ላይ የተፈፀመውን ጥቃትና የአገር ክህደት በመተው በተቃራኒው አሸባሪውን ቡድን ደግፎ መዘገቡን አስታውሳ በኢትዮጵያ ላይ የሀሰት ዘገባውን ቀጥሏል ብላለች።

አንዳንድ ምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያን በተመለከተ ከአንድ አመት በላይ ሳይታክቱ በሁለት ጉዳዮች ላይ አነጣጥረው ሲዘግቡ እንደነበርም ጠቅሳለች።

የኢትዮጵያ መንግስት ሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ ፍቃድ አልሰጠም እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት አባላት እርዳታ የጫኑ መኪኖች እንዳይንቀሳቀሱ አግደዋል በማለት ከእውነታው የራቀ ዘገባ እየሰሩ መሆኑን ጠቁማ ለምን ይህንን አደረጉ ስትል ትጠይቃለች፡፡

የአሜሪካ መንግስት ነጻነትንና ነጻ ሀገር መሆንን በአግባቡ ማየት አለመፈለጋቸው እንደ ዜጋ አግራሞትን ፈጥሮብኛል ስትልም አና ተናግራለች፡፡

ይህ ሁሉ በመሆኑ የፀጥታው ምክር ቤት በአሜሪካ ተፅእኖ ስር የወደቀ መሆኑን በማስረዳት ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ጉዳይ የተሳሳተ አቋም የሚያራምደው ለዚሁ እንደሆነ ትጠቅሳለች።

የአፍሪካ ችግር በአፍሪካውያን መፈታት እንደሚችል በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል የምትለው ጋዜጠኛ አና በዚህ ዙሪያ ሩሲያ እና ቻይና የሚያራምዱት አቋም ትክክል መሆኑን አስረድታለች።

ከዚህ ጉዳይ በተያያዘ የአሜሪካ ህግ መወሰኛ ምክር ቤት የኢትዮጵያን እውነታ በአግባቡ በመገንዘብ ያሳየው ነገር መልካም ጅምር መሆኑንም ጠቅሳለች።

በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በተደራጀ መንገድ የኢትዮጵያን እውነታና የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃንን ሀሰተኛ ዘገባ ለማጋለጥ እያደረጉት ያለው ዘመቻ አስደናቂ መሆኑንም ተናግራለች፡፡

በሳን ፍራንሲስኮ የምንትቀሳቀሰው አና ጋሪሰን በብላክ አጀንዳ ሪፖርት ላይ አምደኛ ስትሆን በከተማዋ በሚገኙት ሳን ክራንሲስኮ ቤይ ቪው፣ ብላክ ስታር ኒውስ፣ ካውንተር ፓንች፣ ግሎባል ሪሰርች እና ፓሲፊክ ራዲዮ ላይ ጽሁፎቿን ታቀርባለች፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም