ጀርመን ለኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠየቁ

53
አዲስ አበባ ነሀሴ 18/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጀርመን የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ሚኒስትር ገርድ ሙለር የተመራውን የልዑካን ቡድን ዛሬ በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ። የጠቅላይ ሚኒስትሩና የጀርመን መንግስት ልዑካን ቡድን ውይይት ትኩረትም የሁለትዮሽ ግንኙነትና የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ጉዳዮች እንደነበር ውይይቱን የተከታተሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍፁም አረጋ ለኢዜአ ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለልዑኩ በአጠቃላይ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላም ለማምጣት እየተደረገ ያለውን ጥረት አስመልክተው ማብራሪያ መስጠታቸውን ነው ያመለከቱት። በተለይም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ለረጅም ጊዜ ተፈጥሮ የቆየውን አለመግባባትን በመፍታት ወደ ሰላማዊ ግንኙነት የመጡበትን መንገድ ለልዑካኑ ማብራራታቸው ተመልክቷል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በኢኮኖሚያዊና ፖሊቲካዊ ጉዳዮች ላይ እያካሄደች ስላለው ሪፎርምም ገለጻ ማድረጋቸውንም አቶ ፍጹም አክለዋል። የጀርመን መንግስት ለኢትዮጵያ እየሰጠ ያለውን ድጋፍ በተለይም በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ እንደዚሁም በግብርና ልማት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል። በተለይም ግብርናን በማዘመን ረገድ ጀርመን የተሻለ ልምድ ያላት አገር መሆኑዋን አመልክተው፤ ይህንንም ወደ ኢትዮጵያ ለማስረጽ በተሻለ መልኩ ድጋፋን እንድትቀጥልም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያመለከቱት። በዚህና በተለያየ ዘርፍ ያላትን ድጋፍም አጠናክራ እንድትቀጥል በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል። የጀርመኑ የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ሚኒስትር ገርድ ሙለር በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ እየተፈጠረ ላለው የሰላምና መረጋጋት ኢትዮጵያ በተምሳሌትነት ተጠቃሽ ናት። በተጨማሪም ኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላማዊ ጉርብትና በፍጥነት መጀመራቸውን ያደነቁት ሚኒስትሩ፤ በሁለቱ አገሮች መካከል የቀጥታ በረራ በመጀመሩ መደሰታቸውን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በወሰዳቸው የለውጥ አርምጃዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ የመጣው ውጤት የሚያስደንቅ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል። በአካባቢው በአሁኑ ወቅት የሚታየው ለውጥ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑንም ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም