የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመመከት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው

45

ታህሳስ 7/2014 /ኢዜአ / በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለውን የውጭ ጣልቃ ገብነት ለመመከት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ተናገሩ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምዕራባውያን አገራት በሌሎች አገራት በተለይም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት በተመለከተ የፓናል ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ፕሮፌሰር ካሳሁን ብርሃኑ፤ በኢትዮጵያ ላይ የውጭ ጣልቃ ገብነት በከጥንት ጀምሮ የነበረ መሆኑን አስታውሰዋል።

ጣልቃ ገብነቱ ከአክሱማዊ ዘመነ መንግሥት መጀመሩን ገልጸው በተለይም በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የፖርቹጋልና የኦቶማን ቱርክን ጣልቃ ገብነት እንዲሁም በ19ኛውና በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ጫናው መበርታቱን ተናግረዋል።  

በእነዚህም የታሪክ ሂደቶች ውስጥ ከግብጽ ጀምሮ ኃያላን የምዕራባውያን አገራት መሳተፋቸውን ጠቁመው ጣልቃ ገብነቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅሟን የሚገዳደር መሆኑን ነው ያነሱት።       

አሁን ደግሞ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል አሸባሪው ህወሃት የከፈተውን ጦርነት ተከትሎ አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም አገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ በተለያየ መልኩ ጣልቃ እየገቡ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይም የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ፣ ኖርዌይ፣ አየርላንድ መንግሥታት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ አግባብ ያልሆነ ጣልቃ ገብነት መፈጸማቸውን ተናግረዋል።    

በኢትዮጵያ ላይ በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ ምዕራባውያን አገራት የሚደረገው ጣልቃ ገብነት ዋነኛ ዓላማው የተወሰኑ ቡድኖችን ጥቅም ለማስከበር መሆኑን አስረድተዋል።  

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርት ቤት ዲን ዶክተር ጌታቸው አሰፋ፤ አንዳንድ የምዕራባውያን አገራት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ተገን አድርገው በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል ብለዋል።

አገራት በሌሎች አገራት የውስጥ ጉዳይ እንዳይገቡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር፣ የአፍሪካ ኅብረት ቻርተርና የሄልሲንኪ መመሪያ በግልጽ ቢደነግጉም አገራቱ ሕጎችን በማን አለብኝነት እየጣሱት መሆኑን ተናግረዋል።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ብሊንከን፣ በመንግሥታቱ ድርጅት የአሜሪካ ቋሚ ተወካይ ሊንዳ ቶማስ በተለያዩ ጊዜያት ያደረጓቸው ንግግሮች  ዓለም አቀፍ ጣልቃ ገብነትን የሚከለክሉ ሕጎችን በግልጽ የሚሽሩ መሆኑን አስረድተዋል።   

ይህም ማለት "የአንድን አገር መንግሥት፣ ተቋምና ሌሎች አካላትን ስምና ክብር ማጠልሸት ነው" የሚለውን ዓለም አቀፍ ሕግ  መጣሱን የሚያሟላ መሆኑን አንስተዋል።

በተጓዳኝም ተ.መ.ድ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1981 ጣልቃ ገብነት ማለት "የአንድን አገር የፖለቲካ ሥርዓት ማወክና የሰብዓዊ መብትን ጉዳይ ለጣልቃ ገብነት አብዝቶ ማጮህ" የሚለውን ውሳኔም በተግባር አሳይቷል ብለዋል።

በመሆኑም መንግሥት በተለይም ተመሳሳይ ችግር የደረሰባቸውን አገራት በማስተባበር በእነዚህ የምዕራባውያን አገራት ላይ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ማድረግ እንዳለበት አስረድተዋል።

በተጓዳኝም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም በመገናኛ ብዙሃን የማስገንዘብና የማሳወቅ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም