በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ኮሪደር 40 ኢንዱስትሪዎች በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ጉዳት ደርሶባቸዋል

94

ታህሳስ 7/2014 /ኢዜአ/ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በኮምቦልቻ የኢንዱስትሪ ኮሪደር 40 ፋብሪካዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለፀ።

በደረሰው ጉዳት ከ11 ሺህ በላይ ዜጎች ከስራ ገበታ ውጭ ሆነዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አሸባሪ ቡድኑ ባደረሰው ውድመት በባለሃብቶች እና በሰራተኞች ላይ ኢኮኖሚያዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን በማሰማራት ፋብሪካዎች ላይ ከፈጸመው ዘረፋና ውድመት ባሻገር ፋብሪካዎቹን በጦር ካምፕነትና ምሽግነት ተጠቅሟል ብለዋል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ የዘረፋቸውን ንብረቶች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ታርጋ በለጠፉ መኪኖች ማመላለሱንና ኀብረተሰቡን አስገድዶ ወደ ፋብሪካዎች በማስገባት እነርሱ የዘረፉ አስመስሎ በካሜራ መቅረጹን ተናግረዋል፡፡

የዘረፋቸውን ተቋማት ሰነዶች ማጥፋት ሌላው በአሸባሪ ቡድኑ የተፈጸመ ውድመት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ጉዳት በደረሰባቸው በ40 ኢንዱስትሪዎች  በተደረገው ጥናት ስምንቱ ከፍተኛ ውድመት የደረሰባቸው በመሆኑ በአጭር ጊዜ ወደስራ መመለስ እንደማይችሉም ነው ያብራሩት።

ሌሎች ስምንት ፋብሪካዎች መካከለኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን 24ቱ ደግሞ ጥገና ተደርጎላቸው ወደ ስራ መመለስ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

በዚህም  ከ11 ሺህ በላይ ሰራተኞች ከስራ ገበታ ውጭ ሆነዋል ነው ያሉት፡፡

አሸባሪ ቡድኑ የፈጸመው ጉዳት ትውልዱን በኢኮኖሚ በመጉዳት አገር የማፍረስ ዓላማ ያነገበ መሆኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴሩ የወደሙ ኢንዱስትሪዎች ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ ስራ በሚመለሱበት ጉዳይ ላይ  ከኮምቦልቻ ከተማ አሰተዳደርና ባለሃብቶች ጋር ውይይት ማድረጉንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በዚህም ድጋፍ የሚሰጡ ባለሙያዎችን  ወደ ስፍራው ለማሰማራት እና የተቋረጡ የመሰረተ ልማቶች ስራ እንዲጀምሩ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር ስምምነት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም