የተለያዩ ተቋማት በአፋር ክልል ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የአይነት ድጋፍ አደረጉ

60

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 07/2014(ኢዜአ) የተለያዩ ተቋማት በአፋር ክልል በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የአይነት ድጋፍ አደረጉ።

ድጋፉን ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እንዲሁም የኢንደስትሪ ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋሞቻቸው ጋር በመተባበር ነው፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ በዚህን ወቅት የአፋር ህዝብ የአሸባሪው ህወሃት ቡድን ወረራን በመመከት ረገድ ለሰራዊቱ ያሳየው ደጀንነት የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በሽብር ቡድኑ የወደሙ የውሃ እና የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን መልሶ በመገንባት ኀብረተሰብን ተጠቃሚ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም ነው የገለጹት፡፡

የሚኒስቴሩ ከዚህ ቀደም ለመከላከያ ሰራዊቱ የ10 ሚሊየን ብር የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፤ በዛሬው እለትም በአሸባሪ ቡድኑ ወረራ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚገመት የአይነት ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

የኢንደስትሪ ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ብርሃኑ ሰርጃቦ በበኩላቸው የሚኒስቴሩና የተጠሪ ተቋማት የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች "ለወገን ደራሽ ወገን ነው" በሚል 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት የአይነት ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ ተቋማቱ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም