በኢትዮጵያ ላይ የተሸረበው ሴራ በሌሎች የአፍሪካ አገራት ላይ ሲፈፀም የቆየ ክፉ ተግባር ነው

97

ታህሳስ 7/2014/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ ላይ የተሸረበው ሴራ በሌሎችም የአፍሪካ አገራት ላይ ሲፈፀም የቆየ ክፉ ተግባር መሆኑን ኬኒያዊው የህግ ባለሙያና የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኙ ላቪኒአ ሚሊአ ተናገሩ።

አፍሪካ ከውጭ የሚመጣባትን ያልተገባ ጣልቃ ገብነት ፈፅሞ መቀበል የለባትም ብለዋል።


ኬኒያዊው የህግ ባለሙያና የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኙ ላቪኒአ ሚሊአ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አፍሪካ ያልተገባ ጣልቃ ገብነት ለሚያደርጉ ምዕራባውያን መንበርከክ የለባትም ብለዋል።

በኢትዮጵያ ላይ የያዙት ተገቢ ያልሆነ አቋምና ጣልቃ ገብነት አስደንጋጭና አስገራሚ መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ በሕገ መንግስታዊ ስርዓት የተመረጠ ሕጋዊ መንግስት ያላት አገር መሆኗን ሊያውቁ ይገባል ነው ያሉት።

የአሜሪካ መንግስትም ይሁን አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት ለኢትዮጵያ ህዝብ በጎ ነገር ቢያስቡ ኖሮ ሕጋዊውን መንግስት መደገፍ ነበረባቸው ብለዋል።

ኢትጵያውያን በህጋዊ መንገድ የተመረጠ መንግስት እንዳላቸው በርካታ ኬንያውያን በመረዳታቸው የምዕራባውያኑን ጣልቃ ገብነት የሚያወግዘውን የበቃ ዘመቻ #NoMore  መቀላቀላቸውንም አስረድተዋል።

አንዳንዶቹ የምዕራቡ ዓለም አገራት "ላይ ላዩን ለእውነትና ለሰብዓዊነት የቆሙ ቢያስመስሉም እውነታው ግን እሱ አይደለም" ይላሉ ላቪኒአ ሚሊአ።

የእነርሱ ሃሳብና ፍላጎት በሽብር ተግባር ላይ የተሰማራውን ሕወሓት ወደ ማዕከላዊ መንግስት ስልጣን መመለስ ነው ሲሉም አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ላይ የተሸረበው ሴራ በሌሎች የአፍሪካ አገራት ላይ ለዓመታት ሲፈፀም የቆየ ተመሳሳይ ክፉ ተግባር መሆኑንም ገልጸዋል።

የአፍሪካን ነፃነት የሚያቀነቅነው የቀድሞ የቡርኪናፋሶ መሪ ቶማስ ሳንካራ ግድያ የክፉ ተግባራቸው አንዱ መገለጫ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሊቢያ፣ በአፍጋኒስታን፣ በሶሪያና ኢራቅ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ስም ብዙ ጥፋቶች ተፈፅመዋል፤ አገሮቹም እስካሁን ሰላምና መረጋጋት እንደራቃቸው ናቸው ብለዋል።

የአፍሪካ አገራት በትግላቸው ከቅኝ ግዛት ነጻ ቢወጡም የእጅ አዙር ቅኝ ግዛቱ መቀጠሉን ጠቅሰው አህጉሪቷን ከተፅእኖ ለማስወጣት የቀድሞው የጋና ፕሬዚዳንት ኩዋሜ ኑኩሩማህ እና ሌሎችም የፓን አፍሪካ አቀንቃኝ መሪዎች የጀመሩትን አንድነት ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም