የሲዳማ ክልል በሁሉም ግንባሮች የድርሻውን ይወጣል

68

ሀዋሳ፤ ታህሳስ 7/2014 (ኢዜአ) የሲዳማ ክልል ሀገርን ለማዳን እየተካሄደ ያለው የህልውና ዘመቻ በስኬት እንዲጠናቀቅ በሁሉም ግንባሮች የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይን አስመልክቶ  ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ አሸባሪው ህወሓት በአማራና አፋር ክልሎች በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ  ዘግናኝ ጭፍጨፋ ፈጽሟል፤ አፈናቅሏል፤ የሀብት ዘረፋና መሰረተ ልማቶችን አውድሟል።

የአሸባሪውን  ህወሓት የጥፋት  ተግባር መመከት የሞት ሽረት ጉዳይ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ ሀገርን ለማዳን እየተካሄደ ያለው ዘመቻ በስኬት እንዲጠናቀቅ ክልሉ በሁሉም ግንባሮች  የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።

ሀብት ማሰባሰብ፣ስንቅ ዝግጅትና አቅርቦት፣የአካባቢን ሰላም ማስጠበቅ ፣ ተፈናቃይ ወገኖችን መደገፍ፣የዘማች ቤተሰቦች እንክብካቤ፣ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል ርእሰ መስተዳደሩ።

አቶ ደስታ እንዳመለከቱት፤ የሲዳማ ክልል ህዝብ  አሸባሪውን ሀይል ለመመከት እየተደረገ ባለው ተጋድሎ ልጆቹን መርቆ ወደ ግንባር በመሸኘት እየተሳተፈ ይገኛል።

በተለያዩ ጊዜያት የገንዘብና የዓይነት ድጋፎችን በማሰባሰብ ለሚመለከተው አካል እንዲደርስ መድረጉን ጠቅሰዋል።

የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋምና የደረሰውን የንብረት ውድመት ለመተካት የሲዳማ ክልልና ህዝብ ከወንድም እህቶቹ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን አስፈላጊውን ሁሉ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል  አስታውቀዋል። 

የሲዳማ ህዝብ ክልል ለመሆን ያቀረበው ጥያቄ  በአሸባሪው ህወሓት ለዓመታት ሲገፋ መቆየቱን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ ክልሉ ዛሬ ላይ ራሱን በራሱ ማስተዳደር በመጀመሩ በአካባቢው ያለው ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱንም አውስተዋል።

ሰላምን ይበልጥ  በማጠናከር የክልሉ መንግስትና ህዝብ ከአጎራባች ክልሎች ጋር ተስማምቶ መኖር መጀመሩን ጠቁመዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች የጸጥታ ችግር ሲያጋጥም ከአጎራባች ክልሎችና ህዝቡ ጋር ተባብሮ መስራት በመቻሉ በአሁኑ ጊዜ በክልሉ ያለው ሰላም ለኢንቨስትመንትና ለሌሎች የንግድ ስራዎች ተመራጭ እንዳደረገው አስረድተዋል።

ሰላሙን ቀጣይ ለማድረግም ህዝብና አመራሩ ተናቦ ከመስራቱ ባለፈ ከአጎራባች ክልሎች ጋር ያለውን ትስስር ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አሸባሪውን ለመመከት በሚደረገው የህልውና ዘመቻ የመከላከያ ሠራዊቱን ለመደገፍ የክልሉ ህዝብ በዓይነትና በገንዝብ ድጋፍ ማድረጉን ያወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይህ ተግባር ዘመቻው በስኬት እስኪጠናቀቅ ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በውጭ  የሚኖሩ  ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት እየደረሰ ያለውን ተጽዕኖና ጣልቃ ገብነት ለማስቆም  አንድ ሆነው እያደረጉት ያለው የበቃ ንቅናቄ ዘመቻ  የሚያኮራ መሆኑን ጠቅሰዋል አቶ ደስታ።

የበቃ ንቅናቄ ዘመቻው  ኢትዮጵያውያን ቀደም ብሎ እንደነበረው የተከፋፈሉ ይሆናሉ የሚል የተሳሳተ ግምት የነበራቸው አሸባሪው ህወሓትና የአንዳንድ ምዕራባዊያን  መገናኛ ብዙሃን ተቋማት ጭምር ያስደነገጠ መሆኑን አመልክተዋል።

 በሁሉም የአለም ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሚያደርጉት የበቃ ዘመቻ  እንቅስቃሴ ኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ እንዲል  እያደረጉት ላለው አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

"ገናን በኢትዮጵያ እናክብር” በሚል በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት የሚመጡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ለመቀበል ክልሉ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የህልውና ዘመቻውን በስኬት በማጠናቀቅ ዘላቂ የሆነ ኢትዮጵያዊ አንድነትና የማይናወጥ ሀገራዊ ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ትግል የሲዳማ ክልላዊ መንግስትና ህዝብ የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም