ጦርነቱ ኢኮኖሚው ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመታደግ የልማት አማራጮች ላይ መረባረብ ይገባል

65

ሃዋሳ ታህሳስ 6/2014(ኢዜአ) ጦርነቱ በኢኮኖሚው ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመታደግ የተለያዩ የልማት አማራጮች ላይ መረባረብ ያስፈልጋል ሲሉ የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

በዩኒቨርሲቲው የምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪ አርጋው አመሎ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ጦርነት ከሚያደርሰው ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት በተጨማሪ የሀገር ኢኮኖሚን የሚጎዳ ነው።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ተገዳ የገባችበት ጦርነት የአገር ኢኮኖሚን በእጅጉ እንዳይጎዳ መንግስትና ዜጎች በተለያዩ የልማት አማራጮች ላይ ሊረባረቡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለመደገፍ ከሚያስችሉ ወሳኝ እርምጃዎች መካከል የግብርና ልማት ዘርፍ ቁልፍ መሆኑን የጠቆሙት ምሁሩ፣ በዘርፉ ምርታማነትን በማሳደግ የውጭ ጫናውን መቋቋም እንደሚቻል ገልጸዋል።

"በተለይ አሜሪካና አንዳንድ የምዕራባዊያን አገራት በእጅ አዙር እየተካሄደ ባለው ጦርነት የኢትዮጵያን አልገዛም ባይነት ሰብሮ ለማንበርከክ የሚያደርጉትን ሴራ በአግባቡ መገንዘብ ያስፈልጋል" ብለዋል።

እንደ መምህርና ተመራማሪ አርጋው ገለጻ፣ በማደግ ላይ ያለውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በማዳከም አገሪቱ ወደኋላ እንድትጓዝ አሜሪካንን ጨምሮ የአንዳንድ ምእራባዊያን አገራት ጫናዎች እየበረቱ ነው።

እንዲህ ያለውን ጫና በመቋቋም አገርን ከአደጋ ለመጠበቅና በአሸናፊነት ለመውጣት ራስን ለመቻል በሚያስችሉ የልማት ሥራዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

"ያለንን አማራጭ ሁሉ አሟጦ ለመጠቀም የምንነሳበት ወሳኝ ጊዜ ነው" ያሉት ምሁሩ ዜጎች በራስ አቅምና ዕውቀት አገርን ማሳደግ እንደሚቻል ግንዛቤያቸውን ማሳደግ እንደሚገባ መክረዋል።

የምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪው እንዳሉት ስንዴንና ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በትኩረት ሰርቶ ኢኮኖሚውን መደገፍ ያስፈልጋል።

በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንም ገንዘባቸውን በባንክ ብቻ በመላክ ጥቁር ገበያውን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ተባባሪ እንዲሆኑም ምሁሩ አስገንዝበዋል።

በጦርነቱ ምክንያት እየተጎዳ ያለውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለመጠገን እንዲቻል የዜጎችን የቁጠባ ባህል ማሳደግ እንደሚገባም ነው የገለጹት።

ኢትዮጵያ በሉአላዊነቷ ከሚመጣ አካል ጋር ቁጭ ብሎ የሚደራደር መሪ በታሪኳ እንዳልነበራት የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የንግድ ህግ መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር ዮሐናን ዮካሞ ናቸው።

ይህም ቱባ ማንነቷ ሳይበረዝ እንዲኖር ከማስቻሉ ባሻገር ለአንዳንድ ምዕራባዊያን ራስ ምታት ሆኖባቸው እንደቆየ አስታውሰዋል።

ጦርነቱን ተከትሎ የሚከሰቱ የተለያዩ ችግሮችን ለመቋቋም ሀገር በቀል ዕውቀት ከመጠቀም ባለፈ የአገር ሀብትን ማወቅና ሥራ ላይ ማዋል ዋነኛ ስልት መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ጠንካራ የስራ ባህል ማዳበር ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ምሁሩ "በተለይ በፍጥነት እያደጉ ካሉት ከቻይናና መሰል ሀገራት ልምድ መውሰድ ያስፈልጋል" ብለዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር ዮሐናን እንዳሉት ምዕራባዊያን የምስራቅ አፍሪካ ቀንድ አካባቢን ለመቆጣጠር ያላቸውን ፍላጎት ለማሳካት ኢትዮጵያን ማንበርከክ ግባቸው ነው።

"ይህ እንዳይሆን ኢትዮጵያዊያን በያዝነው አቋም በመጽናት፣ በኢኮኖሚውም ይሁን በሌሎች ጉዳዮች የውስጥ ችግሮቻችንን የመፍታት ልምዳችንን በማዳበር የመደራደር አቅማችንን ማሳደግ የጊዜው  አንገብጋቢ ጉዳይ ነው" ብለዋል።

እንዲሁም አገሪቱ የዘረጋችውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም በአፋጣኝ መተግበር፣ የማዕድን ዘርፉን ማዘመንና በስፋት በመጠቀም የህልውና ዘመቻው የሚያስከትለውን የኢኮኖሚ ጫና ለመቋቋም መትጋት እንደሚገባ ምሁራኑ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም