የህልውና ዘመቻው በድል እስኪቋጭ ድጋፋችንን እንቀጥላለን

88

ድሬዳዋ፣ ታህሳስ 7/2014 (ኢዜአ) የህልውና ዘመቻው በድል እስኪቋጭ ድረስ በገንዘባቸውና በእውቀታቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ መምህራን አስታወቁ።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከ2ተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

መምህራኑ በወቅቱ እንደተናገሩት ህወሃት ከውልደቱ እስከ አሁን በኢትዮጵያና በዜጎች ላይ ታሪክ የማይሽረው ጥፋትና ውድመት አድርሷል፡፡  

አሸባሪው ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር እየፈጸመ ያለው አገር የማፍረስና ዜጎች የመጨፍጨፍ ተግባር  አረመኔ ቡድን መሆኑን ማረጋገጫ መሆኑን ተናግረዋል።  

"ለአገርና ለዜጎች ጠንቅ የሆነን ሽብርተኛ ቡድን በተጀመረው በህብረ ብሄራዊ አንድነት ዘመቻ ተረባርቦ ማስወገድ ይገባል" ብለዋል፡፡

‹‹ህወሃት እንደ ድርጅት መሸነፍ አለበት›› ሲሉ መምህራኑ አመልክተዋል፡፡

የህልውና ዘመቻው በድል እስኪቋጭ በገንዘባቸውና በእውቀታቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ  አስታውቀዋል፡፡

መምህራኑ የኢትዮጵያን በአለም አቀፍ ደረጃ የዲፕሎማሲ አሸናፊነት ለማረጋገጥ በጀግኖች ኢትዮጵያዊያን የተጀመረውን አለም አቀፍ ንቅናቄ ለማጠናከር ተግቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በተለይ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ  በውጭ አገራት ያሉ ኤምባሲዎች ላይ የጀመሩት የለውጥ ሥራዎችን ይበልጥ በማጽናት በዲፕሎማሲው መስክ የተሻለ ውጤት  ለማምጣት መስራት እንደሚገባ  አመልክተዋል፡፡

በተመሣሣይ የድሬዳዋ የንግዱ ማህበረሰብ በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባካሄዱት ውይይት የኢትዮጵያን ህልውና ለማረጋገጥ እየተካሄደ የሚገኘው ዘመቻ በአሸናፊነት እስኪደመደም የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡

የሁሉም ነገር መነሻና መድረሻ አገርና ሰላም ሲረጋገጥ በመሆኑ ለነዚህ ተግባራዊነት ያላቸውን ገንዘብ፣ ሃብት፣ እውቀትና ቁሶች እስከመጨረሻው በሥራ ላይ እንደሚያውሉ አስታውቀዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም