ምርምሮች የተጠናከረ ሥነ-ምግባርን እንዲከተሉ እየተሰራ ነው

694

ጎባ፣ ታህሳስ 07/2014 (ኢዜአ) በሀገሪቱ ምሁራን የሚካሄዱ ምርምሮች የተጠናከረ የሥነ-ምግባር መመሪያን በመከተል ለሀገርና ለዜጎች ይበልጥ ጥቅም እንዲሰጡ እየሰራ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴሩና በመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ትብብር የተዘጋጀ የምርምር ሥነ-ምግባር መሠረታዊያን ስልጠና ለዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች ተሰጥቷል፡፡

የአቅም ግንባታ ስልጠናው ላይ በሚኒስቴሩ የሣይንስና የምርምር ጉዳዮች ዳይሬክተር 

ጄነራል ዶክተር ሰለሞን ቢኖር እንዳሉት፤ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሁራን የሚከናወኑ የምርምር ሥራዎች የተጠናከረ ስነ-ምግባርን ያከበሩ መሆን አለባቸው።

የሚካሄዱ ምርምሮች በሰው ልጅ፣ እንስሳትና አካባቢ ሥነ-ምህዳር ላይ አንዳችም ተፅዕኖ መፍጠር እንደሌለባቸው አመልክተዋል።

“ምርምር ሥነ-ምግባርን ካልተከተለ ተፅዕኖው ከባድ ነው” ያሉት ዶክተር ሰለሞን ችግሩ እንዳይከሰት ብሔራዊ የምርምር ሥነ-ምግባር ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን አውስተዋል።

በመላው ሀገሪቱ የሚካሄዱ ምርምሮች ለሀገርና ለዜጎች ይበልጥ ጥቅም እንዲሰጡ

 ለማስቻል የተዘጋጀ ወጥ የሆነ ሀገር አቀፍ የምርምር ሥነ-ምግባር መመሪያ ላይ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አህመድ ከሊል በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማሩ ተግባር በተጓዳኝ የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግርና ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ምርምሮችን እያካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

“ለዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች የተሰጠው የምርምር ሥነ-ምግባር የአቅም ግንባታ ሥልጠና ስኬታማ የምርምር ውጤት ለማስመዝገብ ይረዳል” ብለዋል፡፡

የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በአስር ዓመቱ  የስትራቴጂክ ዕቅዱ በግብርና፣ ቱሪዝምና በጤናው ዘርፍ የሚካሄዱ ምርምሮችን በማጠናከር የልህቀት ማዕከል ለመሆን ግብ አስቀምጦ እየሰራ መሆኑን ከዩኒቨርሲቲው የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡